ቀለድሁና ሳቅ ብትል
ደማም አፏ፥
እንደበቃ ባህታዊ፥
(የረቀቀውን አጉልቶልኝ
የጠበበውን አስፍቶልኝ)
ጠሐይቱ ከዓይኖቿ ማይ፥
ተነካክራ ተለቃልቃ ፥ ስትመለስ ወደሰማይ፥
ዐየሁና... ዐየሁና...
በልጅነት በውብ ዘመን ፥ ድሮ እንደሰሙት ሙዚቃ፥
ሆድ ውስጥ ያለ ባር ባር የሚል ፥ ከሰመመን የሚያነቃ፥
የሚመስል፥
በአሳሳቋ ንፅህና፥
የረሳሁትን መኖር ፥ ደሞ ደሞ አስብና፥
እናፍቅና... እናፍቅና...
አሳሳቋ፥
ከዐይኖቿ ጋር ቅንብሩን፥
የተሳካ ስብጥሩን፥
ፊት ገጿ ላይ የሚራቀቅ ፥ የተፈጥሮን ፍልስፍና፥
አጠናና... አጠናና...
"ትንኝ ልሁን?
ተወርውሬ ፥ ከብሌኗ ስር ልወተፍ?
የዓይኖቿን በር ደጅ ልጥና?
ይለይለት ሞት ይውሰደኝ ፥ ጨው እንባዋን ልጠጣና?"
እል እልና...
አሳሳቋ እንደባህር ዛፍ ፥ ሌላ ቁንጅና ሲገድል፥
ጎኗ ያለውን ውበት ሁሉ ፥ የሌላ ማማር ሲያጎድል፥
የብቻዋን ልዕልና
እታዘብ... እታዘብና...
ከሳቋ ፊት ተቀምጬ
አያታለሁ... አያታለሁ
"ምንሆንክ?"ስትል
"ቀልድ በሆንሁ" እላታለሁ
ቀልድ ልሁንልሽ?
ገጣሚ ሚኪ ምናሴ