来自 ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖 (@bookshelf13) 的最新 Telegram 贴文

ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖 Telegram 帖子

ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖
"ስለመጻሕፍት ከመጻሕፍት መንደር እንዘምራለን!"
18,903 订阅者
2,716 张照片
24 个视频
最后更新于 27.02.2025 06:07

ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖 在 Telegram 上分享的最新内容


ልብወለድ የአዋቂዎች ተረት ተረት አይደለም።

ህፃናት ከንባብ ጋር የሚተዋወቁት በተረት መፃህፍት ነው። የተረት መፅሀፍት ታሪክ ነጋሪዎች ናቸው። ለጋ ወጣቶችም በብዛት የሚያነቡት ልብወለድ መፃህፍትን ነው—በተለይ genre fiction የምንላቸውን። ልብወለዶች በተለምዶ በሁለት ይከፈላሉ—genre fiction እና literary fiction ተብለው።

በአማርኛ እቅጩን የሚገልጽ ትርጉም የላቸውም። በቀላሉ ለመግለፅ ያህል ዠነር ፊክሽን ከገፀባህሪ ይልቅ ለሴራ ቦታ የሚሰጡ፣ ስነፅሁፋዊ ፋይዳቸው እምብዛም የሆነ፣ አስፈሪ፣ የፍቅር፣ የስለላ፣ ልብ አንጠልጣይ ወዘተ እየተባሉ የሚከፋፈሉ ናቸው። ሊተራሪ ፊክሽን ደግሞ ስነፅሁፋዊ እሴታቸው እጅግ የላቀ፣ የቋንቋ ውበታቸው የረቀቀ፣ ከሴራ ይልቅ ለገፀባህሪ አትኩሮት የሚሰጡ ናቸው። እውነተኛ ልብወለድ የሰው ልጅ ነፍስ ጥናት ነው። ከሰው ልጅ ነፍስ የበለጠ ርእስ ደግሞ የለም። ታዲያ በሳል አንባቢዎች ለምን የልብወለድ ንባብን ገሸሽ አድርገው በኢልብወለድ ንባብ ይጠመዳሉ? ለምንድነው ልብወለድ ያልበሰሉ ለጋ አንባቢዎች ምርጫ ሆኖ የቀረው?

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ቀላል አይደለም። ቢሆንም ልብወለድን ልብ የወለደው፣ ተራ ቅዠት አድርጎ የመመልከት አባዜ አለ። በመጀመሪያ የትኛውም የልብወለድ ደራሲ መቶ በመቶ የፈጠራ ታሪክ ሊፅፍ አይችልም። የልብወለዱን ገፀባህርያት የሚስለው ከራሱ፣ በአካባቢው ካሉ ሰዎች፣ በአጠቃላይ በእውኑ አለም ከሚያውቃቸው ሰብጀክቶች ነው። ታሪኩንም ቢሆን በዙሪያው ከሚያየው፣ ከሚሰማው፣ ከሚከናወነው ተነስቶ ነው። ታላቅ ደራሲን ከሌሎቻችን የሚለየው የምናውቀውን አሮጌ ነገር እና ታሪክ በለዛ አጅቦ፣ በቋንቋ አስውቦ ስለሚያቀርብ ነው። እውነተኛ ባለ ተሰጥኦ ደራሲ የተለመደውን አዲስ፣ አዲሱን ደግሞ የተለመደ የማድረግ ረቂቅ ችሎታ ያለው ከያኒ ነው። ከዚህም ባሻገር አስተዋይ አይን፣ ረቂቅ ምናብ የታደለ ነው። የምናውቀውን እውነት አድሶ ሲነግረን አፋችንን በአድናቆት ከፍተን እንሰማዋለን።

ታሪክ ነገራ ከሁሉም የስነፅሁፍ አይነቶች ለሰው ልጅ መንፈስ ቅርብ ነው። አንባቢም ደረቅ እውነት በብዛት ማንበብ ይቸከዋል። የልብወለድ ንባብ አስደሳችና መልእክቱም ከአንባቢ መንፈስ ጋር ለረዥም ግዜ ተጣብቆ የሚቀር ነው። ችግሩ ያለው አሳማኝ፣ ተነባቢ፣ ከራሳችን ህይወት ጋር በቀላሉ ልናቆራኘው እና ልናዛምደው የምንችለው የልብወለድ ታሪክ መፅሀፍ ለመፃፍ ቀላል አይደለም። ታላቅ ችሎታ ይጠይቃል። እጅግ የተዋጣላቸው የልብወለድ ታሪክ ፀሀፊዎች ጥቂት ናቸው። ለአብነት ዶስቶቭስኪን፣ ሂዩጎን፣ ዲክንስን፣ ቶልስቶይን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ደራሲዎች የሰውን ነፍስ ገላልጠው ራቁቱን የማየት የረቀቀ ብቃት አላቸው። ያዩትን በለዛ እና በተዋበ ቋንቋ የመግለፅ ተሰጥኦ አላቸው። የሚፈጥሯቸው ገፀባህርያት ከተአማኒነታቸው የተነሳ ከመፅሀፍ ገፅ አምልጠው በመካከላችን የሚኖሩ ያህል እንዲሰማን የሚያደርጉ ናቸው። የልብወለዶቻቸው ሴራ ሽንቁር የለውም። የተወለዱትም ከተራ ቅዠት ሳይሆን ከታላቅ መንፈስ ነው። ትጉህ አንባቢ እንደዚህ አይነት ጥበብ የጠገቡ ልብወለዶችን መርጦ ቢያነብ በቀላሉ ከልብወለዶች ጋር በፍቅር ይወድቃል።

ስታትስቲክስ እንደሚያሳየው በየአመቱ ከሚታተሙት ሁሉም መፃህፍት መካከል 80% ልብወለዶች ናቸው። ይሁን እንጂ ከነዚህ መሀል አብዛኛዎቹ ዠነር ፊክሽን ናቸው። ስነፅሁፋዊ ውበት የተላበሱ ቁምነገረኛ ሊትራሪ ልብወለዶች በቁጥር ጥቂት ናቸው። እነዚህ ልብወለዶች ለገበያ አያመቹም። ከፍተኛ የሽያጭ ሪከርድ አያስመዘግቡም። እሴታቸው ትልቅ ተፈላጊነታቸው ትንሽ ነው። ገበያው በእርካሽ ዠነር ፊክሽን ስለተጥለቀለቀ በሳል አንባቢዎች ፊታቸውን ወደ ኢልብወለድ አዙረዋል። ነገር ግን እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ከሰው ልጅ ነፍስ የበለጠ፣ የረቀቀ ርእስ የለም። የታላላቅ ልብወለዶች ዋነኛ ርእስም የሰው ልጅ ነፍስ፣ የሰው ልጅ ስነልቦና ነው። አዋቂ አንባቢዎች ይህንን ታላቅ ርእስ ገሸሽ አድርገው የኢልብወለድ ንባብ ላይ ተጠምደዋል። የታላቁን ፍጡር የሰው ልጅ ነፍስ ችላ ብለው የሰው ልጅ መገልገያ የሆኑ ተራ ቁሶች ላይ አተኩረዋል።

የሰው ልጅ በሳይንስ እጅግ ተራቅቆ አተምን ሰንጥቋል፤ በስነህይወት የሴልን ፍጥረት መርምሯል፣ የዲኤንኤን ሚስጥር ደርሶበታል፤ ወደ ጨረቃ ተጉዟል፤ ኒውክለር ቦምብ ሰርቷል። በጀኔቲክ ኢንጂነሪንግ፣ በሮኬት ሳይንስ፣ በናኖቴክኖሎጂ ተመንጥቋል። ይሁን እንጂ ከሁሉም የረቀቀ የእውቀት ክፍል ከነዚህ አንዱም አይደለም። ከሁሉም የጠለቀ፣ የረቀቀ፣ የገዘፈ ርእስ የሰው ልጅ ስነልቦና ነው። ስነልቦና የሰውን ነፍስ የሚያጠና ሳይንስ ነው(በግሪክ psyche ማለት ነፍስ ሲሆን psychology የነፍስ ጥናት ነው)

ሳይንስ እስከ አሁን ስለ ሰው ልጅ ስነልቦና የሚያውቀው እፍኝም አይሞላ። ቸር እንኳን እንሁንለት ቢባል የሳይንስ እውቀት ከ10% አያልፍም። ስነልቦና እጅግ የተወሳሰበ ሳይንስ ነው። በተጨማሪ ደረቅ የስነልቦና ኢልብወለድ መፃህፍት ይህንኑ እውነት በአግባቡ መግለፅ አይችሉም። ሊተራሪ ፊክሽን የሚመጡት እዚህ ጋር ነው። ከኢልብወለድ የስነልቦና መፃህፍት ይልቅ ሊተራሪ ፊክሽን የሰውን ልጅ ስነልቦና በመግለፅ የተዋጣላቸው ናቸው።

በምሳሌ ላስረዳ። ግባችን በውቅያኖስ ውስጥ መዋኘት ነው ብለን እንነሳ። ኢልብወለድ የስነልቦና መፃህፍት በዚህ ተምሳሌት ውስጥ የዋና መመሪያ(swimming manual) ናቸው። የፈለግነውን ያህል የዋና መመሪያ መፃህፍት ብናነብ ዋናተኛ መሆን አንችልም። ለመዋኘት ምን ማድረግ እንዳለብን እናውቃለን። ግን ድንገት ውሃ ውስጥ ተነስተን ብንገባ በተአምር ካልሆነ መዋኘት አንችልም። ሊተራሪ ፊክሽን የሚመጡት እዚህ ጋር ነው። ልብወለዶች ልክ እንደ ሲሙሌሽን ናቸው። ምናባዊ አለም አላቸው፤ ገፀባህርያት እና መቼት አላቸው፤ ታሪክ አላቸው። ራሳቸውን የቻሉ ሚጢጢ ህይወት ናቸው። እዚህ ውስጥ ገብቶ ዋና መለማመድ ይቻላል። እንደ ውቅያኖሱ ሰፊ እና ጥልቅ ባይሆኑም መዋኘት ለሚፈልግ በቂ ናቸው። ስነፅሁፋዊ ልብወለዶች 100% እውነተኛውን አለም ባይሆኑም በሰው ልጅ ነፍስ ዙሪያ ለመዋኘት በቂ ናቸው። የሰውን ልጅ ስነልቡና ለመረዳት ያስችላሉ። በዚህ ስሌት የዶስቶቭስኪ ልብወለዶች እያንዳንዳቸው 100 ደረቅ የስነልቡና መፃህፍትን ከማንበብ ይልቃሉ። የሰውን ነፍስ ራቁቷን ተገላልጣ ሲያሳያችሁ አጀብ ያስብላል። በነገራችን ላይ ታላቁ የስነልቦና ጠበብት እና የሳይኮአናሊሲስ ፈጣሪ ሲግመን ፍሪይድ የዶስቶቭስኪ ግርፍ ነው። ፍሩይድ ዶስቶቭስኪን አንብቦ ነው ስለ ነፍስ የተረዳው። ፅንሰሃሳቦቹንም ያፈለቀው ከዚያ ወዲህ ነው። ይህ ያልተለመደ ነገር ነው። በስነፅሁፍ፣ ስነልቦና እና ፍልስፍና አለም የተለመደው ፈላስፋው ወይም ሳይኮሎጂስቱ ቀድሞ ነው የሚወለደው። ከዚያ ደራሲው ፍልስፍናውን ያነብና ከማረከው ፍልስፍናውን በሚፅፈው ልብወለድ ውስጥ ያንፀባርቃል። በፍሩይድ እና በዶስቶቭስኪ ግን የሆነው የተገላቢጦሽ ነው። ቀድሞ ደራሲው ተወለደ። ሳይኮሎጂስቱ ልብወለዶቹን አነበበ። በልብወለዱ ሃሳብ ተነሳስቶ አነጋጋሪ ፅንሰሃሳቦቹን አረቀቀ። ታዲያ ዶስቶቭስኪን አታደንቀውም?! ወንጀልና ቅጣት፣ የካራማዞቭ ወንድማማቾች፣ የስርቻው ስር መጣጥፍ፣ ቁማርተኛው፣ ብርሃናማው ሌሊት፣ ድሃ ሰዎች፣ ዘ ኢዲየት፣ ዘ ፖሰስድ ሁሉም ድንቅ የዶስቶቭስኪ ልብወለዶች ናቸው። ደራሲውን ጨምረህ የምታደንቀው ደራሲው ከሞት ፍርድ ያመለጠ፣ ወደ ሳይቤሪያ ለአምስት አመት ተግዞ ከባድ የቅጣት ስራ የሰራ፣ እነዚያን ውብ

ልብወለዶች የፃፈውም ከቁማርተኝነቱ እና ከሚጥል በሽታው ጋር እየታገለ መሆኑን ስትረዳ ነው። አንድ ደራሲ መርጠህ ማንበብ ብቻ ካለብህ ዶስቶቭስኪን አንብብ። አንድ ልብወለድ ብቻ ማንበብ ካለብህ የካራማዞቭ ወንድማማቾችን አንብብ።

አንድ ሌላ ታላቅ ደራሲ ልጨምር። ደራሲው ብዙ መፃህፍት ቢኖሩትም ያነበብኩት አንዱን ብቻ ነው። ታዲያ ይህ ልብወለድ እጅግ የተዋጣለት በመሆኑ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ። መፅሀፉ ወደ አማርኛ እንኳን በሶስት የተለያዩ ደራሲዎች ተተርጉሟል—ችግረኞቹ፣ መከረኞቹ፣ ምንዱባን። በሬዲዮ ተደጋግሞ ተተርኳል። ወደ ብዙ አለም አቀፍ ቋንቋዎች ከተተረጎሙ ድንቅ የፈረንሳይ የስነፅሁፍ ሃብቶች አንዱ ነው። በመድረክ፣ በፊልም ተደጋግሞ ተሰርቷል። ደራሲው ቪክቶር ሂዩጎ ይባላል። የመፅሀፉ የፈረንሳይኛ ርእስ Les Miserables ይባላል። ርእሱ ራሱ ዝነኛ ከመሆኑ የተነሳ ወደ እንግሊዝኛ ሲተረጎም እንኳን እንዳለ ነውንጂ በእንግሊዝኛ ተመጣጣኙ The Miserables ተብሎ አይተካም። በእርግጥ እንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ተቀራራቢ በመሆናቸው ብዙም ልዩነት የለውም። ለማንኛውም ይህ ልብወለድ ሁሉም ቁምነገረኛ አንባቢ ሊያነባቸው፣ ሊደጋግማቸው፣ ሊከልሳቸው ከሚገቡ ጥቂት ውድ የአለም ስነፅሁፍ ሃብቶች ዋነኛው ነው። እንደውም አንድ አንባቢ ሲያዳንቅ መከረኞቹን የፃፈው ቪክቶር ሂዩጎ አይደለም። እራሱ እግዚአብሔር ከሰማይ ወርዶ የፃፈው የሁላችንም የምድር ጎስቋሎች ታሪክ ነው። እኔም በተምሳሌታዊ አገላለፁ እስማማለሁ። ገፀባህሪያቱ በምናብ የተፈጠሩ ሳይሆን አጥንትና ደም፣ ስጋና ነፍስ ያላቸው ተአማኒ በሁለት እግራቸው የሚራመዱ ሰዎች ናቸው። ዣንቫልዣ፣ ፋንቲን፣ ኮዜት፣ ዣቪየር ሁሉም የእውኑ አለም ሰዎች መሳይ ናቸው። በጣም ተአማኒ ከመሆናቸው የተነሳ ከነገፅታቸው፣ ከነባህሪያቸው ከተነበቡ ከብዙ አመት በኋላ እንኳን ወለል ብለው ይታወሳሉ፤ አይረሱም። የደራሲው ብእር ሃያል ነው። ልብወለዱ የአለምን አስቀያሚነት፣ ፍትህ አልባነት፣ የሰዎችን ጨካኝነት እና ሩህሩህነት፣ የፍቅርን መጥፋት ብቻ በአጠቃላይ በእውኑ የምናውቃትን አለም ለዛ ባለው ብእራቸው እንዳለ ቁጭ አድርገዋታል። ይሄም ሁሉም አንባቢ ደጋግሞ ሊያነባቸው ከሚገቡ ግሩም መፃህፍት መሀል አንዱ ነው።

የመጨረሻ ምርቃቴ ደግሞ Gone With the Wind ነው። በእርግጥ የዚህ ልብወለድ የፊልም ቨርዥኑ ጆርጅ ፍሎይድ በዘረኛ ፖሊስ ከተገደለ በኋላ በግፊት ከኔትፍሊክስ ስትሪሚንግ ሰርቪስ በዘረኝነት ተወንጅሎ እንዲወርድ ሆኗል። በእርግጥ ልብወለዱ እዚህም እዚያም ዘረኛ ጭብጦች አሉት። ነገር ግን ሁለት ነገሮችን ግልፅ ማድረግ እፈልጋለሁ። በመጀመሪያ የልብወለዱ አብይ ጭብጥ ዘረኝነት አይደለም። ልብወለዱ ስለ ጦርነት አስከፊነት እና ስለ ጠንካራው የሰው ልጅ መንፈስ ነው። የትኛውም አንባቢ ከራሱ ህይወት ጋር በቀላሉ አቆራኝቶት ሊዝናናበት፣ ሊማርበት ይችላል። ሁለተኛው ጉዳይ አሁንም ቢሆን እጅግ የተማሩ ዘረኛ ሰዎች በመሀከላችን አሉ። ዘረኝነት ክፉ በሽታ ነው። ለማጥፋትም ረዥም ግዜ ይፈልጋል። ይህንን መፅሀፍ ማንበብ ስላቆምን ብቻ ዘረኝነት ከመሀከላችን ተጠራርጎ አይጠፋም። እንደዚያም ሆኖ መፅሀፉ የተጋነነ ዘረኝነት አለው ብዬ አላስብም። ደራሲዋ በመፅሀፏ ያንፀባረቀችው የነበረውን ዘረኝነት ነው። እንዲያውም በመፅሀፉ ውስጥ ዘረኛ እሳቤው ባይካተት ጎደሎ ይሆን ነበር። ሰዎች ፍፁም አይደሉም፤ እንከን አላቸው። ያንን እንከናቸውን እየገደፍን የምንፅፍ ከሆነ ደራሲ ሳይሆን ፕላስቲክ ሰርጅን እየሆንን ነው። ተአማኒ ነገር ለመፃፍ ሰዎችን ከነእንከናቸው፣ ከነብጉራቸው መሳል አለብን። በእርግጥ ደራሲዋ ያንፀባረቀችው የገፀባህሪያቱን ዘረኝነት ብቻ ሳይሆን የራሷንም ጭምር ነው። ታዲያ ይሄኮ ብዙ አይገርምም። ለዘመናት ባሮችን እየፈነገሉ ሲሸጡ የነበሩት የተማሩ አውሮጳውያን እና አሜሪካውያን ዘረኛ ነበሩ። ቅኝ ግዛትን ያስፋፉትም እንደዚሁ። ስድሰት ሚሊየን አይሁዳውያንን በመርዝ ጋዝ የፈጁት እጅግ የተማሩ ጀርመናዊያን ነበሩ። አሁንም በምሁር ካባ የተሸፈነ ዘረኝነት አለ። የነጮቹ መፅሀፍ ውስጥ ብናገኘውም ያን ያህል ሊደንቀን አይገባም። አሁንም በማስመሰል ፈገግታ የተሸፈነ ዘረኝነት ሞልቷል። መፅሀፍ ውስጥ ስናገኘው እንክርዳዱን ከስንዴው ማጣራቱ የአንባቢ ፋንታ ነው። ወደ መፅሀፉ ስንመለስ የደራሲዋን የትረካ ብቃት አለማድነቅ አይቻልም። መፅሀፉ ብዙ ንግግር(dialogue) የለውም። ደራሲዋ የመረጠችው አብዛኛውን ታሪክ በትረካ መንገር ነው። የትረካ ችሎታዋ የተዋጣለት በመሆኑ አንባቢ ሳይሰለች ብዙ ገፆችን በአንዴ ፉት ሊያደርግ ይችላል። ይህ መፅሀፍ ለመፃፍ አስር አመት ፈጅቷል። እንዲሁ ለመተርጎም አስር አመት ፈጅቷል። አስገራሚ ግጥምጥሞሽ! ይሄን ያህል አመት ፈጅቶ ባይበስል ነው የሚገርመው። ገፀባህሪያቱ እዚህም የማይረሱ ናቸው—እስካርሌት ኦሃራ፣ ሬት በትለር፣ አሽሌ ዊክስ፣ ሜላኒ ሃሚልተን። ልብወለዱ እንዲህ ይላል። ሬት በትለር እስካርሌት ኦሃራን አፈቀረ፣ እስካርሌት አሽሌ ዊክስን ፈቀደች፣ አሽሌ ሜላኒ ሃሚልተንን አገባ። የአራት ሰዎች የፍቅር ህይወት ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሆነ። ይሄ መግቢያ ብቻውን ልብወለዱን ለማንበብ አጓጊ ያደርገዋል። ልብወለዱ ግን ከእስካርሌት እና ሬት ፍቅር የላቀ ነው፤ ከተራ የፍቅር ሰንሰለት የጠለቀ ነው። ልብወለዱ ስለ መራራ የህይወት ገፅታ ነው። ልብወለዱ ስለማይበገረው የሰው ልጅ መንፈስ ነው።

የሰርቫንቴስን ዶን ኪኾቴ ልብወለድ በማንበብ ይህን ያህል ስቄ አላውቅም!ዶን ኪኾቴ ከመጠን በላይ የጦረኛ ልብወለድ መጽሀፍትን ያነበበ የልብወለዱ ዋና ገጸባህሪ ነው። ጎረቤቶቹ ዶን ኪኾቴ ብዙ በማንበቡ አእምሮው ተነክቷል ብለው ያስባሉ። እሱ ግን ማንንም ከቁብ ሳይቆጥር አሮጌ ጥሩሩን ለብሶ ፣ ፈረሱን ሮሲናንቴ ተፈናጦ አሽከሩን ሳንቾ ፓንዛን አስከትሎ ፣ እመቤት ዱልሲናን በልቡ ይዞ ያነበባቸው መጽሀፍት ላይ እንዳሉት የማይታመኑ ገድሎች ለመፈጸም ይወጣል።

ስፔን እነሆ ከ400 አመት በኋላ እንኳን “ዶን ኪኾቴ”ን የሚተካከል የስነጽሁፍ ስራ የላትም።

ዶን ኪኾቴ ሁላችንንም ነው። ለራሳችን ያለንን የተጋነነ አመለከት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የከንቱ ምኞታችንን ስፋትና ጥልቀት ለፍላጎታችን ምርኮኛና እስረኛ መሆናችን ሁሉ ይከስትልናል። ይሄ ሁሉ በተለያየ መልኩ ይገለጻል። የእያንዳንዱ ወንድ የፍላጎት ማረፊያ የምትሆንም አንዲት ሴት አትጠፋም።

ሁሉም አንባቢ እነዚህን አራት ታላላቅ ልብወለዶች ደጋግሞ እንዲያነብ እጋብዛለሁ።

📚📚📚

ልብወለድ ማንበብ ግዜ ማባከን ነው የሚሉ ሰዎች አጋጥመውኛል። ልብወለድ ህልመኛ የሚያደርግ፣ ለተጨባጩ አለም ህይወት ምንም የማይጠቅም፣ ደራሲው በዘፈቀደ የፃፈው ተረት ተረት ነው ይላሉ።

በሌላ በኩል ጥናት እንዲህ ይላል

፩) በየአመቱ ከሚሸጡ እና የሚነበቡ መፅሀፍት 80% ልብወለዶች ናቸው

፪) ልብወለድን ማንበብ የራስንም የሌሎችን አመለካከት ለመረዳት ቁልፍ ነው። በአጭሩ ልብወለድ ስለ ሰው ነው። አብዛኛዎቹ ኢልብወለድ መፅሀፍት(ሁሉም አይደለም) ከሰው ውጪ ስላለ ነገር ነው። ታድያ እራስን ሳያውቁ በቢሊዮን የሚቆጠር የብርሃን አመት ላይ ስለሚገኝ አለም ለመረዳት መሞከር ከንቱ አይደለም!

፫) ልብወለድ በሚነበብበት ወቅት የአእምሮአችን ኤሌክትሮኬሚካል ስርአት ይቀየራል። ይህም በተጨባጩ አለም ለሚገጥመው ነገር ንቁ እና ቀልጣፋ ምላሽ ይሰጣል።

፬) ለአምስት ደቂቃ ብቻ እንኳን ልብወለድ ማንበብ ውጥረት እና ጭንቀት ይቀንሳል። አእምሮ በተጨባጩ አለም የገጠመውን ችግር ረስቶ ለግዜውም ቢሆን በሌላ አለም ውስጥ ይመሰጣል። ከተመስጦው ሲነቃ አእምሮው ስለተረጋጋ በእውኑ አለም የገጠመውን ችግር በቀላሉ ይፈታል።

፭) ይሄኛውን ለማመን ቢከብድም ተመራማሪዎች ልብወለድ ማንበብ ህይወት ይቀጥላል ብለዋል።

በአጠቃላይ አንድ ደራሲ እንዳለው ልብወለድን ማንበብ በየግዜው አዳዲስ አለማትን መተዋወቅ ነው። በነዚህ አዳዲስ አለማት ውስጥ አንባቢው የራሱን የተወሳሰበ አለም ያያል። ምክንያቱም ልብወለዶች ሌላ ምንም ሳይሆኑ የራስን ነፍስ የሚያሳዩ መስታወት ናቸው። ምናልባት ጥሩ መስታወት ያልገጠማቸው ሰዎች ቆንጆ ልብወለድ አልገጠማቸውም ማለት ነው። ልብወለድ ጠቃሚ ነው ማለት ሁንሉም አይደለም። እንደውም በብዙ እርካሽ ልብወለዶች ተጥለቅልቀናል። ሁሉም ኢልብወለድ መፅሀፍት ጥሩ እንዳልሆኑ ሁሉ ልብወለድም እንዲሁ ነው። የምናነበውን መምረጥ አለብን። ጃኪ ኮሊንስ እና ጃኩሊን ሱዛን የቸከቸኩትን አንብቦ ልብወለድ አይጠቅምም ማለት አያስኬድም። እነዚህ እርካሽ ተብለው የሚቆጠሩ ልብወለዶች እንኳን ለለጋ ወጣቶች ከፍተኛ የመዝናናት ስሜት ተመራጭ ናቸው። ስለዚህ እንደ እድሜያችን የምናነበውን መምረጥ አለብን። የልብወለድ አለም ራሱ ሰፊ ነው። በብዙ የሚቆጠሩ ዘውጎች አሉት። የተለያየ ባክግራውንድ፣ ባህል፣ ስነልቡና የሚፃፉ ናቸው። የዲክንስንም፣ የአቼቤን፣ የስቴፈን ኪንግን፣ የጄ ኬ ሮውሊንግንም በአንድ ጨፍልቆ ማየት አይገባም። ሁሉም ለተለያየ አንባቢ ትርጉም ይሰጣል። በ20 አመት እና 40 አመት አንድ አይነት ልብወለድ አናነብም። ጉዞ ላይ ለመዝናናት የምንመርጠው ቀለል ያለ ልብወለድ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከተለያየ አንፃር መርጠን ማንበብ አለብን።

📚📚📚

ብዙ ሰዎች ልብወለድን ተረት–ተረት እያሉ ሲያናንቁት ስሰማ ያስቀኛል። የእውቀት ዘርፎችን እንደ ሽንኩርት አንድ በአንድ እየላጣችሁ መሀሉ(core) ላይ ብትደርሱ የምታገኙት ስነ–ልቦናን (psychology) ነው።

የማይጠቅም እውቀት የለም። ታሪክ፣ሳይንስ፣ሂሳብ በአጠቃላይ የቁስ ሥልጣኔዎች ሁሉ የሰው ልጅ አእምሮ ስራ ውጤቶች ነው። የሰው ልጅ አእምሮ ስለፈጠራቸው ነገሮች ይህን ያህል ትኩረት ከሰጠን ስለ አእምሮ፣ስለ ሰው ልጅ ራሷ/ራሱ ምንኛ የበለጠ አንሰጥም። ስለ አእምሮ ስል ኒውሮሳይንስ እያልኩ አይደለም። ስለ ሰው ልጅ ስል ስለ ስጋው እያልኩ አይደለም― ስለ ስነልቦናችን ማለቴ እንጂ!

ምክንያቱም እኛ የስነ ልቦናዎቻችን ውጤት ነን―በግልም፣በቡድንም። "You are not what you think you are. What you think, you are!" እኛ እያንዳንዳችን የአስተሳሰባችን ድምር ውጤት ነን፤አለም የሁላችንም አስተሳሰብ ድምር ውጤት ነው። ስነ ልቦና ደግሞ የሰውን አስተሳሰብ የሚያጠና ሳይንስ ነው፤የሰውን ነፍስ የሚያጠና ዘርፍ ነው። ምክንያቱም psyche ነፍስ ማለት ነው። "We are not human beings with spiritual experience. We are spiritual beings with human experience."

እኛ ነፍስ ነን፤ስጋው ቅርፊት ነው። ስጋውን ቀርፋችሁ ብትጥሉት የምታገኙት ነፍስ ነው። ነፍስ አይቀረፍም። ስነ–ልቡና ይህንን ነፍስ ነው የሚያጠናው። ሌላው እውቀት ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣ ነው። ስነልቡና የእውቀት ሁሉ ቁንጮ ነው። የሰው ልጅ ስነልቦናን ከተረዳችሁ jackpot አሸነፋችሁ ማለት ነው።

ታዲያ ልብወለድ እዚህ ውስጥ ምን ጥልቅ አደረገው ሊባል ይችላል? ስነልቦናን በደረቁ ለመተንተን መሞከር አሰልቺ ሊሆን ይችላል። የተፈለገውን ሀሳብ በምሉእነት ለመግለፅ አቅም ያጥረዋል። ልብወለድ የሚመጣው እዚህ ጋር ነው። አያችሁ ልብወለድ የእውነተኛው አለም አነስተኛ ሞዴል ነው። ሁሉም ኢለመንቶች ሪፕረሰንት ይደረጋሉ። እውነተኛው አለም በአውሮፕላን ብንመስለው ልብወለድ ማንበብ የአውሮፕላን simulation ነው።

ልብወለድ ተራም ፣ ተረት ተረትም አይደለም። ምንአልባት ጥሩ ልብወለድ ካላገኛችሁ ጥሩ ሲሙሌተር አልገጠማችሁም ማለት ነው። ለስነልቦና ህይወት የሚሰጠው ልብወለድ ነው። የhuman conditionን ልንረዳ የምንችለው በስነፅሁፍ ነው―ከስነፅሁፍም በልብወለድ። ልብወለድን የሚያክል simulator እስከአሁን የለም። ታላቅ ስነፅሁፍ የልብወለድ እና የስነልቦና ጋብቻ ነው።

© Te Di

[አፍ -ሥግር ልብወለድ ]
| ደራሲ - አዳም ረታ |

©Asrat Yeshi T

እንደመስፈንሪያ

ደራሲ አዳም ረታ ከ1977 ዓ.ም [ ከተደራሲው ጋር የተዋወቀበት እና በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ተከታታዮችና አንባቢዎች ልብ ውስጥ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠበት “አባ ደፋር እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች” በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የታተመው በ1977 ዓ.ም ነው ] ጀምሮ በኢትዮጵያ ስነፅሁፍ ዉስጥ የራሱን ጡብ ለማስቀመጥ የቻለ ከያኒ ነዉ።በ1981 ዓ.ም ከታተመዉ "ማህሌት" ጀምሮ እስከ መጨረሻው ስራ" አፍ" ድረስ አዳም የራሱን ቀለም ሳይለቅ ነገር ግን አከያየኑ በይበልጥም አከያየኑ ዉስጥ ያለዉ ይዘት(content)፣ ቅርፅ( form)፣ አወቃቀር (structural) እና የአፃፃፍ ስልቱ እንዲሁም የስነፅሁፍ ፍልስፍናዉን በተለያየ ቴክኒኮች በመሞከር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየላቀ መምጣቱ ስራዎቹ ምስክር ናቸዉ። ለምሳሌ ከአጫጭር ልብወለድ ስራዎች "ማህሌት፣ከሰማይ የወረደ ፍርፍር" ስራዎች ላይ ቀጥተኛ አተራረክ(Linear Narrate) መንገድ ሲጠቀም የታሪክ ፍሰቱ መስመራዊ እንድርድረት(Linear Momentum)፣ ከጭብጡ ረገድም ልል፣ ቃላት አጠቃቀሙም ጠና ያለ አለመሆኑን ከሌሎች ስራዎች አንፃር ይበየናል፥[ ሌሎች የሚለዉ ግራጫ ቃጭሎች፣ የስንብት ቀለማት፣ እቴ ሜቴ የሎሚ ሽታ እና መዳረሻዬ አፍን ይተካል]። በአዳም ስነጽሑፍ ስራዎች ላይ ርዕሰ ጉዳይ በስፋት በመተንተን አንባቢን ሊያሰለች ይችላል እንጂ ቃላትን የሚራቀቅበት ሐይል ከፈጣሪ የተሰጠዉ ይመስለኛል፤ እንደዉም በቃለመጠይቁ ላይ እምብዛም የማይስተዋለዉ እጁን ከወረቀት ስለሚያናጥቡት ነዉ።

በአዳም የስነፅሁፍ ስራዎች ላይ መቼቱ "ያ ትዉልድ" ሲሆን የአዳም ስራዎችን ተደራሲያኑ ለመረዳት ስለ ያ ትዉልድ ትንሽ ግንዛቤ ሊያደረጅ ይሻል፤ ይህም ተደራሲያኑን የዘመኑን መንፈስ እና መልክ ለመረዳት ያግዛል። በአዳም ስራዎች በስፋት በArchetypal Elements የበለጸገ ነዉ።

"An archetype (ARK-uh-type) is an idea, symbol, pattern, or character-type, in a story. It’s any story element that appears again and again in stories from cultures around the world and symbolizes something universal in the human experience. Archetypes are always somewhat in question. After all, no one has studied every culture in the world – that would be impossible – so we never know for sure whether something is truly universal."

ይመስለኛል አዳም ከመባቻዉ ጀምሮ Archetypal Elements ላይ በአንክሮ ስለሚያስብበት ሐሳቡን እንዳሻዉ እያሽሞነሞነ ይገልፃል፤ መፈከር ይችልበታል። አዳም ጥቃቅን ነገሮችን በቸልታ የሚያልፍ አይደለም። ለአብነት ብናይ
ምሳሌ አንድ፦ #ግራጫ_ቃጭሎች" ላይ ለመዝገቡ ግድ የሚሰጡት "ስለ ናና ከረሜላ፣ ስለጉብታ፣ ስለአበበ ቢቂላ ፎቶ እና አዲስ አበባን ከንፋስ መዉጫ ያስበለጠበት ተረኮች ነገሮች ያለዉን አስተዉሎት ላቅ ያለ ነዉ።

ምሳሌ ሁለት፦ #ይወስዳል_መንገድ_ያመጣል_መንገድ" ላይ የአንድ ሰፈር ልጆች ህይወት እና ዕጣ ፈንታ 7 መንገዶች አድርጐ ይተርካል።በትረካዉ ዉስጥ የልጆቹን ዕድገት፣ ጉርምስና እና የፓለቲካ ተሳትፎአቸው ብሎም አሳዛኝ ፍፃሜን በጥንቃቄ ለሁሉም ሁነት ትኩረት ሰጥቶ ይተርካል።

"ከአንዱ ክፍል ወደ ሌላው ክፍል፣ ከላይ ወደታች ተዟዙሬ አጥንቼአለሁ። ነገሮችን በዐይን፣ በዳሰሳ በጣዕማቸው መድቤአለሁ።

ይሄ ጎዳናዬ ነበር።

ይሄ አገሬም ነበር"

ደሃ እናቱ እንዝርቷን እያሾረች "እግሮችህ የቡሄ ጥቢኛ ይመስላሉ" ትለዋለች። ድህነት ይዟት ለእግሩ ጫማ መግዛት ስለማትችል፣ አድጎ በእግሩ መሄድ ሲጀምር ለእግሮቹ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይጀምራል። የጣቶቹ ቁጥር ጎድሎ እንደሆነ ይቆጥራል፣ ጣቶቹ መሃል ያለውን አቧራ እየፈተለ ይጠርጋል። "በእናቴ የእግሮቼ ጥቢኛ ተብሎ መሰየም መንገዶችን አተኩሬ እንዳይ አደረገኝ" እያለ መንገዶቹን በልዩ አትኩሮት ይመዘግባል።

አዳም በሌላ መልኩ "ያ ዘመን" ላይ ሙጥኝ ያለ ይሆንብኛል።በበርካታ ስራዎቹ በያ ዘመን መንፈስ ጥላ ያጠላባቸዋል፤ ያ ዘመን እንዲረሳ ያልፈለገዉ አንዳች ነገር ይኖራል።[በእርግጥ ይሄን ለማለት psychoanalysis ቢያስፈልገዉም የግል ድምዳሜዬ ነዉ።]

ሥግር ልብወለዱ- አፍ
የደራሲ አዳም ረታ የመጨረሻው ስራ አፍ ሲሆን በ2010 ዓ.ም ለንባብ በቅቷል። "አፍ" ከሌሎች የአዳም ስራዎች ለየት የሚያደርገዉ በድህረዘመናዊ ስነፅሁፍ ቅንብብ ኾኖ በቅርፅ ሐገርኛ ቀመስ የሆነ ሲሆን ይህ በራሱ ለስነጽሁፋችን አዲስ ቅርፅ በማስተዋወቅ ረገድ ወደር የለዉም፤ ይህ ምናልባት ለጀማሪ ከያኒያን ከባህርማዶ ቀድቶ ከማምጣት እንዲታቀቡ ማሳያ ነዉ።

በድህረዘመናዊ ስነጽሑፍ ዉስጥ የተለመደዉን የአፃፃፍ ስልት Deconstructed ማድረግ የተለመደ ነዉ።

"postmodern fiction has obviously changed linearity,linear causality and qualitative difference lose much of thier impact."

አዳም ረታ በ"አፍ ዉስጥ የተጠቀመባቸውን ስነፅሁፍ ዘዴዎችን ለመዳሰስ እንሞክር

1.ቅርጽ
የድርሰቱ ቅርፅ የተቀዳዉ ከባለ አምስት ጠጠር ቅልልቦሽ ጨዋታ ሲሆን እንደጨዋታዉ ድርሰቱም አንዱን[ጌርሳሞት] እንደመቅለቢያ ወደ ላይ አጉኖ ሌሎች አራቶች ጠጠርን[ ገለታ፣ ዘሪሁን፣ባካፋ፣ አቡ] አንድ በአንድ ይሰበስባል።መፅሐፉን ስናነብ ባለአዲስ ቅርጽ መሆኑ ባያጠያይቅም አስቀድመን ቅልልቦሽ ጨዋታ ሕግ ጋር እያስተያየን ማቅረባችን አይቀርም።አዳም ድህረዘመናዊ ስነጽሑፍ የተረዳበት እና ሐገርኛ ጣዕም ለመስጠት የሄደበት ርቀት ይብል ያሰኛል።ከባህላዊ ጨዋታ አንዱ የሆነዉ ቅልልቦሽ በዚህ ልክ አስተዉሎ እንደ አንድ ቅርፅ መጠቀም አስተዉሎት ይጠይቃል።የቅርጹ መልክ ብቻ ሳይሆን አተራረኩ Deduction method መጠቀሙ የቅርጹን ዉበት ጎልቶ አሳይቷል።

2.የቋንቋ እንግዳነት
በድህረዘመናዊ ስነፅሁፍ ላይ ቃላት "the bridge of realm of language and real world" በመሆኑ አዳም ረታ በዚህ ድረሰት ላይ በሰፊዉ አዲስ ቃላትን የተጠቀመ ነዉ። ይህ ምናልባትም አንባቢያን ሊያደናግር ቢችልም ነገር ግን አንባቢያን አገባባዊ ፍቺ (contextual meaning) በመስጠት ዋና መልዕክቱን ማግኘት ይቻላል።

3. ተፋልሶ
በአዳም ረታ በዘመን ዉስጥ ያለዉን የዘመን መልከሸ፣ የዘመን ተጋሪዎች ጋር ተቃርኖ በራስ አዉደምህረት ይብከነከናል። በገጽ (66) "መጠራጠርና መናናቅ ባለበት ቦታ መኖር አይመችም፡፡›› ብሎን ማህበረሰብ አወቃቀራችን እና እንደማህበረሰብ ያለንን settlement ይተቻል፤" ታከተኝ ይለናል። በቀጥሎም በገጽ (36) ላይ "
‹‹በአሉባልታ አገር ላይ ምርምር ምን ይጠቅማል?›› ይለናል።

4.ትረካ ድባብ እና አገባብን(context based)መሰረት ያደረገ መገንዘብ
አዳም በዚህ ድርሰት ዉስጥ ልክ እንደ ቅርጹ በአተራረከሸ ስልቱ ዉስጥ አንዱ የቅልልቦሽ ተጫዋች የሚኖረዉ ሚና እና ለሚቀጥለዉ ለሌላኛዉ እንደሚሰጠዉ ትረካዉንም በሁለት ከፍሎ ይተርካል። የተከፈሉትን ተረኮች ለማየት እንሞክር
መልካ መልክ አንድ(1)

እንደ ጨዋታዉ በመቃለቢያ ጠጠሯ( ጌርሳሞት) የታቦት ማደሪያ ሰፈር ወጣቶችን አንድን ከእንዱ እያቀላለበ በጠጠሮቹ መካከል ግን ያለመያያዝን ይተርካል።ተጫዋቹ መቃለቢያዋን ጌርሳሞት ከፍ አድርጎ በማጎኑ መሬት ያሉትን ጠጠሮች ሳይቀል እንዳንዱ ማለት ከገለታ ጀምሮ ከእጁ እንደወጡ ይተርካል።በዚህ ትረካ ዉስጥም አዳም እያንዳንዱን ሁነቶች በአንክሮ ይተርካል።
መልካ መልክ ሁለት(2)

በዚህ የትረካ ምዕራፍ ዉስጥ ተቀላቢዉ ጠጠር ወደ ላይ ሲያጉት space and time Continue መሰረት አድርጎ የሚኖሩትን ክዋኔዎች ይተርክልናል።

በአጠቃላይ አዳም ረታ በ"አፍ ዉስጥ metafiction፣ በይነ ዲሲፕሊናዊ ጠባይ ያላቸዉ ተረኮች(intertextuality) እና የአዳም የስነጽሑፍ ፍልስፍና የሆነዉን ህፅናዊነት የሆነ stylistic በመጠቀም ዋና ጭብጡ ግላዊ እይታ፣ አንፃራዊ አመለካከት፣ ጥበባዊ ሐሳብ፣ ዉስጣዊ ዉበት ፣ባዶ እዉነት እና ስሜታዊ ዉሸትን ልያሳየን ሞክሯል።

****
📖 አፍ (2010 ዓ.ም)
📖 ግራጫ ቃጭሎች (1997 ዓ.ም)
📖 ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ, አዳም ረታ(2003 ዓ.ም)
📖 The Cambridge Introduction to Postmodernism Fiction, Bran Nicol

የዋጋ ንረት (inflation) መንስኤው እና መፍትሔው
(የQuantity Theory Of Money በመጠቀም የተተነተነ)
=================================

I)  ትርጉም (Definition)

የዋጋ ንረት (Inflation) ማለት ቀጣይነት ያለው የአጠቃላይ ምርቶች እና አገልግሎቶች በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ነው። (Sustained increase in general price of goods & services over aperiod of time)

II) የዋጋ ንረት መንስኤዎቹ (Causes of inflation)

የዋጋ ንረት መንስኤዎች በባህሪያቸው አንድ ወጥ አይደሉም። በየሀገሩ እንደየኢኮኖሚ ባህሪያቸው መንስኤዎቻቸው ይለያያሉ።  የተለያዩ የፖሊሲ ማሻሻያዎች እርምጃዎች እንደሀገሩ ኢኮኖሚ ባህሪና እንደዋጋ ንረቱ መንስኤ ይወሰዳል። የተወሰኑ መንስኤዎችን ለማንሳት

1. የማምረቻ ጥሬ ዕቃዎች  ወጪ ዋጋ ስጨምር የሚከሰት ( Cost push inflation)
2. የምርቶች ፍላጎት መጨመር  የሚፈጥረው የዋጋ ንረት (Demand pull inflation)
3. የመንግስት ወጪ ከመንግስት ገቢ ስበልጥ የበጀት ክፍተትን ለመሙላት በሚታተም ገንዘብ የሚፈጠር የዋጋ የዋጋ ንረት (Deficite induced inflation)
4. ከኢኮኖሚው አቅም በላይ ብድር በማሰራጨት የሚከሰት የዋጋ ንረት ( Credit inflation)
5. ገንዘብን በማተም የሚፈጠር  የዋጋ ንረት (Currency inflation)
በአጭሩ የዋጋ ንረት ከምርት አቅርቦት እና ከገንዘብ ፍላጎት ጋር የሚገናኝ የኢኮኖሚ ክስተት ነው ይህንን አጠር አድርጎ የሚያሳዬን የኢኮኖሚክ ህግ( ቲዎሪ) Quantity Theory of Money (QTM)) ነው።

Quantity Theory of money (QTM) : በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ሁሌም ምርትን በዋጋ ስናባዛ ጋር እኩል መሆን አለበት ይላል። ያለበለዚያ ምርት ሳይጨምር ወረቀቱ ብር ህትመት የሚጨምር ከሆነ ዋጋ መናሩ ግድ ነው ይለናል። በምሳሌ እንየው
               
         Money Supply = Price X Output
                             MV = PY
(M= Money Stock , V= Velocity or Circulation of money, P= Price, Y= Output transacted)

ምሳሌ:- በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ጠቅላላ 1000 ቢሆን እና ምርቶችም 1000 ቢሆኑ ዋጋው 1 ብር ነው ገንዘብን አትመን ብንጨምር ወይም ምርት አምርተን ብንጨምር አልያም ብንቀንስ የዋጋ ንረቱ ምን እንደሚሆን እንመልከት…

            የገንዘብ አቅርቦት = ዋጋ X ምርት
                           1000   = 1 X 1000
ኬዝ አንድ: ምርት ሳይጨምር ወረቀቱ ገንዘብ ቢጨምር ምን ይሆናል
             የገንዘብ አቅርቦት = ዋጋ X ምርት
                            1000   = 1 X 1000
                            2000  =  2 X 1000
                            3000   = 3 X 1000
                            4000  =  4  X 1000
                            5000   = 5 X 1000
ከላይ እንደተመለከትነው ምርት ባልጨመረበት የገንዘብ አቅርቦት የሚጨምር ከሆነ የዕቃዎች ዋጋ ይጨምራል ይህም የዋጋ ንረትን ያስከትላል።

ኬዝ ሁለት:  የብር ኖት አቅርቦት ባይጨምር የምርት እጥረተ ቢኖር ምን ይሆናል
          የገንዘብ አቅርቦት = ዋጋ X ምርት
                            1000   = 1 X 1000
                            1000  =  2 X 500
                            1000   =  5X 200
                            1000  =  10X 100
                            1000   =  20X 50
በኢኮኖሚ ውስጥ የምርት አቅርቦት እያነሰ የሚሄድ ከሆነ የገንዘብ ኖት አቅርቦት ባይጨምርም ከምርት እጥረት የተነሳ የዋጋ ንረት መከሰቱ አይቀርም።

ስለዚህ ኢኮኖሚ ውስጥ የምርት እጥረት ካለ ወይም ኢኮኖሚው ከሚፈልገው በላይ የገንዘብ አቅርቦት ካለ የዋጋ ንረት መከሰቱ ግድ ነው።

III) የዋጋ ንረት መፍትሔው (Policy Measure for inflation)

1. በኢኮኖሚ ውስጥ ከበቂ በላይ ምርት ማምረትና ማቅረብ
          የገንዘብ አቅርቦት = ዋጋ X ምርት
                            1000   = 1 X 1000
                            1000  =  0.5 X 2000
                            1000   = 0.2 X 5000
                            1000  =  0.1 X 10000
    1000 የተለያዩ ምርቶች በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን 10,000 አድርገን ምርታማነትን በግብርና; በኢንዱስትሪ; በአገልግሎት ዘርፍ ብንጨምር 1(አንድ) ብር የነበረው አማካይ የዕቃዎች ዋጋ እስከ 10 ሳንቲም ልወርድ ይችላል። ለዋጋ ንረት ፍቱን መድኃኒት የሚሆነው በኢኮኖሚ ውስጥ የተለያዩ የፍጆታ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ማቅረብ ነው።
2. በኢኮኖሚው አቅም መጠን ገንዘብን ማተም ማሰራጨትና መቆጣጠር።
     
                          የገንዘብ አቅርቦት = ዋጋ X ምርት
                            1000   = 1 X 1000
                            2000  =  1X 2000
                            3000   = 1 X 3000
                            4000  =  1 X 4000
                            5000   = 1X 5000
ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገባው ገንዘብ ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ምርት ጋር መጠኑ ተቀራራቢ መሆን አለበት። በቂ ምርት በሌለበት የወረቀት ገንዘብ አኮኖሚ ውስጥ የምናስገባ ከሆነ ብዙ ብር ትንሽ ዕቃን የመግዛት አቅም ይኖረዋል ይህም ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዲከሰት ስለሚያደርግ ገንዘብ ወደኢኮኖሚ ስሰራጭ የኢኮኖሚውን የመሸከም አቅም ( ምርቶች) መኖራቸውን ታሳቢ ማድረግ ግድ ነው።

ገንዘብን ከኢኮኖሚ የምንቀንስባቸው ዘዴዎች

1. በታክስ ወይም ገቢን አጠናክሮ በመሠብሰብ
2. ቦንድ; የግምጃ ቤት ሰነድ በመሸጥ
3. የቁጠባን ወለድ መጠን ከፍ በማድረግ
4. የብድር ወለዶ መጠን ከፍ በማድረግ
5. የመንግስትን ወጪ ለምርታማነት ስራ ማዋል
6. ሙስናን መቆጣጠር
7. አራጣን ስራን መቆጣጠር

IV) ማጠቃለያ

ከላይ Quantity Theory of Money በመጠቀም የገንዘብ አቅርቦት እና ምርት ምን ያህል ለዋጋ ንረት መንስኤም መፍትሔም እንደሆኑ በቀላሉ ለማስረዳ ሞክሬአለው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ያላቸው አማራጭ በሁሉም ዘርፍ በግብርና በኢንዱስትሪው እና በአገልግሎት ዘርፍ ትርፍ ምርት ማምረት ( Surplus Production ) ስኖር ብቻ ነው። ትርፍ ምርት (Surplus production) ስንል ለ120 ሚሊየን ህዝብ 240 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ለአንድ አመት የሚያስፈልገው የስንዴ ፍጆታ ከሆነ ከ240 ሚሊየን ኩንታል  በላይ ማምረት ማለት ነው። ይህንን

በሌሎች የግብርና ምርቶች እና ኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ማሳካት ስንችል ለዕለት ተዕለት ለፍጆታ የምንጠቀማቸው የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ዋጋ ማንም ጣልቃ ሳይገባ ገበያው በራሱ አማካይ ዋጋ እንዲቀንስ ያደርጋል። በፊዚክስ ሳይንስ የመሬት ስበት (Gravity) ያለው ቦታ በኢኮኖሚክስ ሳይንስ ምርት (Production ) ነው። የመሬት ስበት ከሌለ የዘለለ ሁሉ ወደ ላይ ተንሳፎ እንደሚቀር በኢኮኖሚ ምርት ከሌለ የዘለለ ዋጋ ሁሉ ተንጠልጥሎ ይቀራል እንደመሬት ስበት ወደታች ልያወርደው የምችለው ምርት ብቻ ነው። ለደሀ ሀገር የሞኔታሪ ፖሊሲን እርምጃዎችን (Monetary policy) መጠቀም ብዙም አልመክርም።

መወሰድ ያለበት የፖሊሲ እርምጃ

1. ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ማቅረብ
2. በኢንዱስትሪው እና በአገልግሎት ዘርፍ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ሳቢና ማራኪ የፖሊሲ ድጋፎችን ማቅረብ
3. ሳይታረሱ ፆም የምያድሩ መሬቶችንና ቁጭ ብሎ ስራ አጥቶ የሚለው የሰው ኃይል የሚገናኙበትን የፖሊሲ እርምጃ ማሳወቅ
4. ተቋሞቻችን ምርትና ምርታማነትን ከማደናቀፍ ይልቅ ደጋፊ እንዲሆኑ ማስቻል
5. የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ማንም በሀገሪቱ ውስጥ ተንቀሳቅሶ ማምረት የምችልበት ደረጃ ላይ ማድረስ
6. የመንግስት ተቋማት ከምርት ጋር የተያያዙ የቁጥር ሪፖርቶች ፍፁም ከውሸት የፀዱ ማድረግ
7. ከማምረት; ከማሰራጨት; ከመገበያየት  ድጋፍ ቁጥጥር እና ከግብር አሰባሰብ ጋር የሚገናኙ የመንግስት ተቋማት ፍፁም ከሙስና የፀዱ ማድረግ
8. ዕውቀት መር የመሪነት ስርዓትን ማስተዋወቅ እና መዘርጋት
9. ምርትን ለመጨመረ የተሰራጩ የልማት ባንክ ብድሮችን ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ
10. ኢኮኖሚ ውስጥ በዘፈቀደ የሚገቡ የገንዘብ መጠኖችን ቁጥጥር ማድረግ

መወያያ
አሁን ባለው የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ከላይ በፅሁፉ መሠረት አንድ ኢትዮጲያዊ ግለሰብ ምን አይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት?

© ወንድማገኝ ታዬ
(ፔኪንግ ዩኒቨርስቲ፣ ቤጂንግ ቻይና)

"የገበያውን ሰው ምን ያጮኸዋል ቢሉ እኔ እበላ እኔ እበላ" ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ
በስንዱ አበበ

በዘፈን ግጥም ደራሲያንና በዜማ ደራሲያን አካባቢ በርካታ ችግሮች መኖራቸው ይሰማል።በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦች ያሉትን ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉን ስንሞክር ግን "ስማችን አይጠቀስ" የሚል ምክንያት እያነሱ ጉዳዩን ይሸሹታል።ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ እንዲያነጋግሩን ከጠየቅናቸው ሁሉ መልካም ፈቃዱን በማግኘታችን ልናስተናግደው ተገደናል::

የሁለት ልጆች አባት፤የ50 ዓመቱ ጕልማሳና የበርካታ የዘፈን ግጥም ፀሀፊ ሙሉጌታ ተስፋዬን በጉዳዩ ዙሪያ አወያይተነዋል።

ሪፖርተር፡- በዘፈን ግጥም ፀሀፊያንና በዘፋኞችና በሙዚቃ አሳታሚዎች ዙሪያ ያሉት ችግሮች ምንድን ናቸው ትላለህ?
ሙሉጌታ:- ለምሳሌ ጥፍረ መጥምጥ ቢይዝሽ ፍርንትት አለው። ፍርንትት ማለት ጉያሽ ውስጥ ያብጣል፡፡ ጥፍረ መጥምጡ የያዘሽ ጣትሽ ላይ ሆኖ ሳለ የሰራ ህዋስሽ ይታወካል፡፡ የያንዳንዱ ገጣሚ፣ ሙዚቃ ቤት፣ ዘፋኝ አስተሳሰብ ለጥበቡ ያለው ግንዛቤ ከማነስ የተነሳ ግጭቶቹ ውስጥ ያለው እንከን ፈጥጦ ይወጣል። ግጭቶቹ ደግሞ እኔ እበላ እኔ እበላ ነው::ማዕድ ብቻውን ሲሆን አይሞላም።

ሪፖርተር፡- «እኔ እበላ እኔ እበላውን» ምን ፈጠረው?
ሙሉጌታ፡-በሥነ ጥበቡ ዙሪያ ያሉ ሰዎች የሚገናኙበት አክስሰሪ (አመቺ ሁኔታ) የላቸውም::አይገናኙም። ለየቅል ናቸው።ሁሉም «የደፈጣ ውጊያ» ነው የያዘው። «እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ»ዓይነት፡፡ በጨዋታ መሀል አንቺ ዘና ብለሽ በሰራሽውና በፃፍሽውም ጉዳይ ላይ ከጓደኞች ጋር ስትጫወች'ንኳ ነገ የሚወጣው ካሴት ላይ ያንን ሀሳብሽን ገልብጠው ይለቁታል። ቅንነት የለም፡፡ ንፅህና የለም፡፡ይህ ደግሞ ድንቁርና የሚወልደው ነገር ነው::አለመማር ነው::

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለ የመሰረቅ፣ የመቆንጠር ነገር አጋጥሞህ ያውቃል?
ሙሉጌታ፡- እኔ ከውቅያኖስ ነው የምቀዳው። የፈለገውን ሊወስድ ይችላል፡፡እንደማያልቅብኝ ስለማውቅ ብዙም አልከታተልም::ሀረግ እየተቆነጠረ እንደሚወተፍ አውቃለሁ፡፡ግጥም ከመስራታችን በፊት አንዳንድ ጊዜ ከዜማ ደራሲው ጋር አንድ ላይ ሆነን ዜማውን እሱ እያወጣ እኔ ግጥሙን እየፃፍኩ አብረን እንሰራለን፡፡ ለዜማ መያዣ ተብሎ በሚሰራበት ጊዜ እኔ
«እሄድ እሄድና እላለሁ እረፉ
የጥርሷ ንቅሳት እየታየኝ ዘርፉ» አልልም፡፡ ወደ ህዝቡ ነው የምልከው፤ ህዝቡ ውስጥ የሚፈለፈል ነገር ነው:: ስለዚህ ተጠንቅቄ ነው የምስራው፡፡ ዜማው ተሰርቶ እኔ ግጥሙን ከፃፍኩ በኋላ ሁሉም የየራሱ ሰው አለው::የኔን ግጥም ወስዶ ለሌላ ገጣሚ ይሰጠዋል፡፡እንደ ግነኙነታቸው ማለት ነው።

ሪፖርተር፡- እንዲህ አይነት ነገር በተደጋጋሚ ያጋጥማል?
ሙሉጌታ፡- እጅግ ብዙ ጊዜ ያጋጥማል፡፡
ሪፖርተር፡- ታዲያ አንተ ምን ትላለህ?
ሙሉጌታ፡- ዝም!
ሪፖርተር፡- ገንዘቡስ ይከፈልሀል?
ሙሉጌታ:- ወየው ጉድ! በየት በኩል ነው ገንዘቡ የሚሰጠኝ? የሰራሽበትን እንኳ ሙሉ በሙሉ አይከፍሉሽም፡፡ለምሳሌ የፀደንያን ካሴት ስንሰራ እኔ፣ ፀደንያና ሙሉጌታ አፈወርቅ ሆነን ነው የሰራነው:: ወጪውን የቻለችው ፀደንያ ናት፡፡ውላችን ደግሞ ለሶስት ልንካፈል ነው፡፡አከፋፍልልን ብለን ለአንድ ሙዚቃ ቤት ሰጠነው፡ገንዘቡ ግን በጊዜው ሊሰጠን ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል?
ሪፖርተር፡- አልተዋዋላችሁም?
ሙሉጌታ፡- ውል ቢኖርስ አሁን እንደገጣሚ ስታስቢው ዳኛ ፊት ቆመሽ እንዲህ ተዘርፌያለሁ ብለሽ እሱን ትከራከሪያለሽ? ወይስ ነፍስሽ የተጠለፈችበትን ራዕይ ታሳድጃለሽ? የቱ ጋር ነው የምትቆሚው? ልትታገይ አትችይም፡፡ምክንያቱም ገጣሚ የህዝብ ልጅ ስለሆነ መወገን ያለበት ለህዝቡ ነው፡፡በእንካ ስላንትያ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፡፡ስራውን ለመስራት የሚፈጀው አንድ ቀን ነው።ገንዘቡን ለማግኘት የሚፈጀው ግን የትየለሌ ነው::

ሪፖርተር፡- ይህን የአሰራር ችግር ነው ወይስ ሌላ ምን ልንለው እንችላለን?

ሙሉጌታ፡- አንድ ጊዜ የሆነውን ልንገርሽ::ለአንዱ ዘፋኝ ሁለት ግጥም ሰራሁለት።ዋጋው ላይ አይደለም።
ጉዳዬ የማስተላልፈው መልዕክት ጋር ነው::ግጥሙን ፃፍኩለትና ሞክረው አልኩት፡፡ ይሄኛውን መስመር ቀይርልኝ አለ፡፡መጀመሪያ ስትዘፍነው ልስማህና የሚቀየር ከሆነ እቀይረዋለሁ አልኩት::ምን አገባህ አንተ ከገንዘብህ እንጂ አለኝ፡፡እውነትህን ነው ብዬ ተቀበልኩትና ፊቱ ላይ ቀድጄ ሂድና በፍራንክህ ባርያ የሚሸጥበት አገር ግዛ ብዬ ወጣሁ፡

ሪፖርተር፡- አትግባቡም ማለት ነው?
ሙሉጌታ፡- አስተሳሰባችን ይለያያል፡፡እንደ አስተሳሰባችን ነው፡፡ጉሮሮ የሚውጠውን እጅ አይደለም እንዴ የሚመጥ ነው? እና እንዴት ይደረጋል?

ሪፖርተር፡- ይህ ሁኔታ ታዲያ እስከመቼ ነው የሚቀጥለው?
ሙሉጌታ፡- ይሄ ሁኔታማ ለቀንዳም በሬ ቤት አትከልክሉት ለአመሉ ቀንዱ ይከለክለዋል።ችግሩ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ በዚህ ዙሪያ ያለው ሰው መላ እንምታ ብሎ አንድ ቀን ዘዴ የሚዘይድበት ሰዓት ይመጣል፡፡ ይሰባሰባል፡፡ ይመካከራል፡፡ እኔ ምን የሚገርመኝ እዚሀ ሀገር ላይ የመጨረሻ ድሀ አገር ላይስለምትሰሪው ስራ ይህንን ህዝብ እንዴት ከድህነት እናውጣው ብለሽ ነው የምታስቢው እንጂ ከዚህ ህዝብ ላይ እንዴት አድርጌ የበለጠ ልዝረፈው ብለሽ አታስቢም፡፡ ያለቀለት ህዝብ ነው፡፡ ቆሞ መሄዱም እሱ ሆኖ ነው፡፡ አሁን የፕሬስ ሕጉ ላይ የመብት ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ይህ በዚህ ሰዓት የሚነሳ ጥያቄ ነው?:: በእኔ እምነት ምን አለበት ህዝቡ ይስማው እኛ ልናስብ የሚገባን ነገር እኛ ብርሃን ነን፡፡ አደራ አለብን። በህዝብ ቋንቋ ነው የምንጠቀመው። ከህዝብ ስነቃል፣ ከህዝብ ሳይኮሎጂ ተነስተን ነው የምንሰራው፡፡ እና ወደ ህዝቡ ቢሄድ ለህዝቡ ቢከፋፈል ምን አለበት? ሁሉም ሰው 13 ብር አውጥቶ ኦሪጅናል ካሴት የመግዛት አቅም ላይኖረው ይችላል፡፡አቅሙ ያለው ኦሪጅናሉን ይግዛ፡፡ ይህ የኔ ብጤው ደግሞ በ5ና - በ6 ብር ገዝቶ ይስማ፡፡ ነፍሱ ትታደስ፡ ይማርበት:: ብሶቱን ይከክበት በቃ!

ሪፖርተር፡- ሙዚቃ ቤቶች ለመጭበርበራችሁ ዋነኛ ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ካሴቶች ኮፒ እየተደረጉ በመሸጣቸው ነው የሚሉት፡

ሙሉጌታ:- የሰረቀሽ ቢያፋልግሽ ይገርምሻል? አንዳንዱ ሙዚቃ ቤት ራሱ ኮፒ እያደረገ እየሸጠ እንደገና ኮፒ ተደረገብኝ ይልሻል፡፡ ምኑን ታውቂዋለሽ፡ ሙዚቃ ቤት በራፍ ላይ ኮፒ ተደርጎ ሲሸጥ ያ የሙዚቃ ቤት ባለቤት ግብር ይከፍለበታል ፤ ሊያተርፍ ነው? እበሩ ላይ እየተሸጠ እያየ ዝም ካለ ጠርጥር ከገንፎ አይጠፋም ስንጥር ነው::

ሪፖርተር፡- አንተ በዘፈን ግጥም ሙያ ለተሰማሩ
ወጣቶች ምን ትላለህ?

ሙሉጌታ:- እጅግ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር ወጣቹ ለፈጠራ ስሜት ስላላቸው ፍቅሩ ስላላቸው ግጥም ፅፈው ያመጣሉ:: ወደ ሙዚቀኛው ወደ ዜማ ደራሲው ደርሻለሁ ወይ? እዚህ ላይ ምከረኝ አስተምረኝ ብለው ይመጣሉ:: ግጥማቸውን ይሰጣሉ፡፡ ግጥማቸውን ከሰጡ በኋላ እዚያ ውስጥ ካለው ሀሳብ አፈፍ አድርገው አይረባም ይሉታል ፤ይመለሳል፡፡

ሪፖርተር- ይህንን የሚለው ማነው?

ሙሉጌታ:- ገበያው ውስጥ የገባው ሰውዬ ነዋ!

ሪፖርተር፡- ገበያው ውስጥ ገጣሚ አለ፤ ዜማ ደራሲም አለ፤ ነጋዴም አለ፣ ሁሉም አንድ ናቸው ማለት ነው?
ሙሉጌታ:- መጀመሪያ ሰው ስትሆኚና ሰው ሰው ስትሸቺ ነው በትክክል መስራት የሚቻለው:: ይህንን የምልሽ እኔ በዚህ ውስጥ አልተዘፈቅኩበትም ማለት አይደለም፡፡ እኔም አለሁበት፡፡ እኔም የችግሩ አካል ነኝ፡፡ ግን ችግራችን የሁላችንም ችግር ገና ሰው አልሆንንም:: የሰውኛ አስተሳሰብ በውስጣችን ገና አልሰረፀም፡፡ ባጋጣሚ ቃላት ስለምንሰድር፣ ባጋጣሚ መግጠም ስለቻልን ባጋጣሚ የተለየ ራዕይ ቢኖረንም እኛ የማህበረሰቡ አንዱ አካል አይደለንም፤ ስለዚህ ችግሩ ይመለከተናል፡፡ በጭቃ እየሄድሽ ሱሪዬንና ጫማዬን ጭቃ እንዳይነካው ማለት የሚከብድ ነገር ነው።

ሪፖርተር፡- ይህን ችግር ለመፍታት ምን ይደረግ ቢባል ምን ትላለህ?
ሙሉጌታ:- አሁን ኢንቨስተሮች ሀገራችን እየገቡ ነው:: ብዙ ሀብት ያላቸው ሆቴል ቤት፣ ቡቲክ ይከፍታሉ:: በዚህኛውም ሙያ ደግሞ ትንሽ ልቡን የገዛ፤ ገንዘብ ያለው ሰው ኢንቨስት ቢያደርግ በሃቀኝነት፣ በመግባባት ብንሰራ መፍትሄ ይኖረዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ሞት ከአንገት ሲደርስ ተወደደም ተጠላም ባለጉዳዮቹ ለጉዳያቸው መሰባሰባቸው አይቀርም፡፡ ለዚህ የወንድ በር መስጠት ነው፡፡ ጥያቄዎቹ ሲነሱ ያ ጥያቄ ተብላልቶ መውጫ ቀዳዳ ያበጃል። ሽንት ቤት እንኳን ማስተንፈሻ አለው፡፡ ሞት ካንገት ሲደርስ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ያኔ ይፈታል:: እስከዚያ ድረስ ምንም ማድረግ አይቻልም::

ሪፖርተር፡-ያንተን ግጥም ወስደው ግማሹን የራሳቸውን ጨምረው ሲሰሩት ምን ይሰማሀል? ምንስ ማለት ነው?
ሙሉጌታ፡-ሥራው በሚሰራበት ጊዜ ፊርማ የለም:: ወረቀት የለም:: በመተማመን ነው የምንሰራው፡፡ ከተሰራ በኋላ የኢኮኖሚው ባለቤት የፖለቲካውም ባለቤት አይደለም ፍራንኩን የያዘው ሰውዬ ለገበያው የሚፈልገውንና ለገበያው ይሆነኛል የሚለውን ስሜት ቀስቃሽ የሆነውን ይመርጥና ሌላ ሊወትፍበት ይችላል:: አሁንም ዝም ነው የምትይው::

ሪፖርተር- ፖስተር ላይ ስማችሁ ለምን አይፃፍም?

ሙሉጌታ፦ አሀ! ትደምቂያለሽ! ከደመቅሽ ዛሬ በአንድ ሺህ ብር የምትሰሪውን ስታድጊ ዋጋው ይጨምራል፡፡ ይህቺን ይፈሯታል መሰለኝ።
ሪፖርተር ፦ስማችሁን ላለመፃፍ ምክንያት ይስጡዋችሁዋል?
ሙሉጌታ:- ቀድሞ ነገር ከጉዳይ ይጽፋሻል እንዴ? እንዳንዶቹማ በኪሳቸው ነው የሚያስቡት:: ያንቺን መቃተት፤ ያንቺን ጣር ለመገንዘብ አይፈልጉም:: ነጋዴ (ይቅርታ ይህንን ስላልኩ) የነጋዴ ሀይማኖት ትርፍ ነው:: ማትረፍ ብቻ ነው የሚፈልገው:: አምላክ የባረከው ካልሆነ በስተቀር::
ሪፖርተር፦ ለአንድ ገጣሚ በዚህ ሁኔታ መስራት ምን ማለት ነው?
ሙሉጌታ፦ሰማዕትነት ነው። ምላጭ መዋጥ ማለት ነው፡፡ ገጣሚ ስትሆኚ ለመንገብገብና ለመቃጠል ብቻ ነው የምትፈጠሪው:: ሁላችንም ቢሆን በህይወት ጎዳና ጉዞ ትምህርት ስንጀምር በየክፍሉ አማርኛ ስንማር ግጥም ያልፃፈ የለም:: በተለይ ለአቅመ አዳም ሲደርስ ለወደዳት ላፈቀራት ወዳጁ ግጥም ሊቀኝላት ይፈልጋል:: ሁሉም ሰው ሞክሮታል ሊባል ይችላል፡፡ ግን ገጣሚ የሚሆኑት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። አንድ ፐርስንት ወይም ሁለት፡፡ ግጥም ደግሞ ቃል ነው:: የገጣሚ ህይወት በጣም አስቸጋሪና አስከፊ ነው። አባጣ ገባጣ የበዛበት ነው፡፡ ያንን ቃል የሚያመጣው ከእግዚያብሄር መንፈስ ስለሆነ የግድ ለአደራ እስኪበቃ ድረስ መታሸት አለበት:: ሚልሽያ ሶስት ወር ይሰልጥናል። ፓራኮማንዶ አምስት ዓመት ይስለጥናል፡፡ ለተፈለገው ጉዳይ ማለት ነው::ሰው፤ ተፈጥሮ፣ ፈጣሪ እነዚህ ተዋህደው ቢሄዱ ነው የተፈጥሮ ሕግ የሚመስለኝ። የንቧን ጥዝዝ የሚለውን ድምፅ መተርጎም ስትችይ፤አበባዋንና ንቧን የሚያገኛናቸውን ፍቅር ማሰብ ስትጀምሪ ከሁሉም ጋር ሕይወት ውህደት እስኪኖርሽ ድረስ ያው መታሸት ነው፡፡

ሪፖርተር፦ አንተ እንዴት ነው የምታገኛቸውና ግጥምህን የምትሰጣቸው?
ሙሉጌታ:- እንዳንድ ጊዜ በሙዚቃ ቤቱ በኩል ይመጣሉ፡፡ እንዳንዴ ዘፋኙም ይመጣል፡፡ እንደ ሁኔታው ነው:: ሙሉጌታ ይመቸኛል የሚል ሰው ፈልጐ ያገኘኛል።

ሪፖርተር፦ ለአንድ ግጥም ብዙ ብር ተከፍሎህ ካወቀ ስንት ነው?

ሙሉጌታ፡- በአበበ ተካ ክር 100 ሺህ ብር አግኝቻለሁ፡፡ ዘጠኝ ግጥም ነው የፃፍኩት። ሌላ ቦታ ደግሞ ዘፋኙ ስላሳዘነኝ 200 ብርም ሰርቼ አውቃለሁ። እኔ ፍራንክ ላይ አይደለም ግቤ። በሂሳብ ዋጋ ከወሰድሽው ክፍያ የሚባል አይነት አይደለም:: ስራውን ለመስራት የድገማ ዋጋ ያህል በይው እንጂ ዋጋውማ አይተመንም:: ዘላለም ለሚኖር ነገር አሁን የወፍዬ የምትለዋ ግጥም ዋጋ ስንት ሊሆን ይችላል? በቃ መሄድ ነው:: ሁሉም ጉዳይሽ አይደለም እንዴ? ሀገርሽ ነው፣ ዘመድሽ ነው ጓደኛሽ ነው ያሳደገሽ መንገድ ያመላክትሻል፤ የሸኘሽ አይደል በቃ!

ሪፖርተር- ገጣሚ በመሆንህ ደስተኛ ነህ?
ሙሉጌታ- አንድ ጊዜ የአንድ ገጣሚ ትልቁ ደረጃ ምንድን ነው? ብዬ እሰብኩኝ። ያው ሃሳብ አይደል ስንቃችን? ለምሳሌ እኔና ወዳጄ ፍቅረኛዬ ክፉን በሩቅ ያድርገው እንጂ እሷን እባብ ነድፏት ብትሞት አስቢው ብቻሽን ነሽ፡፡ ታጥቢያትና፤ ታለቅሽና ፤ትገንዥና፤ትቆፍሪና የመጨረሻውን የስንብት ደብዳቤ ግጥም አንብበሽላት ነው የምትሽኛት፡፡እኔ ሳነብላት እቀሰቅሳታለሁ፡፡ ይህን ስሜት ስለሚሰጠኝ እዚህ ድረስ ለመድረስ ነው ግጥም የምፅፈው። ግጥምኮ አስከሬን ይቀሰቅሳል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ለዚህ አደራ መታጨት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ዛሬም ካንቺ ጋር ለማውጋት ያበቃኝ ገጣሚ መሆኔ ነው:: ገጣሚ በመሆኔ እጅግ ደስተኛ ነኝ:: የሚያኖረኝ ግብ አለኝ፡ ለመኖር ሰበብ ሆኖኛል፡ ራዕይ አለኝ። ሃሳብ አለኝ፡፡ ስለዚህ ግር ያለኝ ነገር የለም።ደስተኛ ነኝ።

ሪፖርተር፦ ገንዘብ ግን የለህም
ሙሉጌታ፡- እኔ አሁን «ወፍዬ» የምትለው ዘፈኔን አበበ ተካ ሲዘፍናት ሬዲዮ ላይ ስሰማት ያን ስዓት እኔ አይደለሁ እንዴ ኋገር እየገዛሁ ያለሁት ብዬ አስባለሁ፡፡ አገር የገዛሁ ያሀል ነው የሚሰማኝ። ሁሉም ሰውኮ እኔን እየሰማኝ ነው:: ከዚህ የበለጠ ክብረት ምን አለ ታዲያ?

ሪፖርተር- ሰርተህ ገንዘብ ባለማግኘትህ አይቆጭህም?
ሙሉጌታ፡- ፍትህ'ኮ ሩቅ አገር ነው። ለምሳሌ ቀኝንና ግራ እጅሽን አስተያይ:: ስትፈጠሪ ሁለቱም እኩል ተሰርተዋል፡፡ ሁለቱም እኩል ተሰጥተውሻል ቀኙ ስለጠነ። ግራው ባሪያ ሆነ፡፡ ስለ ፍትህ ስናወራ እውነቱ ሊሆን የሚችለው የሰው ልጅ ቀኙንና ግራውን እኩል ሳያሰለጥን ስለፍትህ ቢለፈልፍ መቼም መቼም የትም አይደርስም፡፡ ፍትህ፣ ቁጭት፣ እልህ ብለን ካልን መጀመሪያ በራሳችን ውስጥ ነው ማረጋገጥ መቻል ያለብን፡፡ አለሙን ለማነጋገር ቀድሞ ራስን ማነጋገርነው ፍትህ፡

ሪፖርተር፦ ኢፍትሃዊ ነገር ላይ ተጠያቂው ማነው ነው የምትለው?
ሙሉጌታ፦ሁላችንም።ሁላችንም አዋጥተናል።
እንደየድርሻችን፡፡ በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል አይደል ነገሩ? እንዱ በጠበጠው ስንል ያልበጠበጠው ጠጣው ማለታችን ነው፡፡ ደፈረሰ ማለት አይደለም። እኔ የሚባል ጨዋታ የለም:: አንቺ ያለ እኔ እኔ ያለ አንቺ መኖር አንችልም፡፡
ምንም እንኳ ከላይ የዘረዘርኳቸው ችግሮች እንዳሉ ቢሆኑም ከሙዚቃ ቤቶችም ሆነ ከከያንያኑ ጥቂቶች አሉ ያዝኑልሻል፡፡ እንኳን የሰራሸውን ሊያስቀሩ ገና ነገ አብረኸን ትስራለህ ብለው ቀድመው በችግርሽ ጊዜ ከጎንሽ የሚቆሙ::እነዚህን ሰዎች በዚህ አጋጣሚ ላመሰግን እወዳለሁ::
አመሰግናለሁ።

ምንጭ፦ © ረፖርተር ጋዜጣ ነሐሴ 20/1994
ሄማንዳ ቴኒ

የሆነ ሰው ሁን፤ ግን ምንም አትሁን!
(Do not be nobody, be somebody!)
(እ.ብ.ይ.)

ማንንም ሰው መሆን ቀላል ነው፡፡ ሌላን ሰው መምሰል አያስቸግርም፡፡ መገልበጥ መኮረጅ አይከብድም፡፡ ራስን መሆን ግን እጅግ ከባድ ነው፡፡ በአስተሳሰብ ራሱን የቻለ፣ የሆነ ሰው መሆን ይከብዳል፡፡ የራሱ ሃሳብ ያለው፣ የራሱ ዓላማ ያለው፣ የራሱ የሚኖርለትና የሚሞትለት ግብ ያለው መሆን ማንንም ሆነ ምንምም መሆን አይደለም፡፡ ራስን መሆን ነው፡፡ ራስን ከመሆን በላይ ትልቅ ዕውቀት የለም፡፡ ብዙዎቻችን ራሳችንን ለመሆን ስለሚከብደን ሌላውን መኮረጅ ነው የሚቀልለን፡፡

አሳቢ ሰው ትርጉም ፈላጊ ፍጡር ነው (Man is simply a being in search of meaning.)፡፡ አይደለም ሌላውን መስሎ ቀርቶ ራሱን ሆኖ እንኳን አይረካም፡፡ የሕይወት ጥያቄ ዘወትር አዕምሮውን ሰላም ይነሳል፡፡ እኔ ማን ነኝ ከሚለው ከባዱ የማንነት ጥያቄ ጀምሮ እስከዕለተ ሞቱ ድረስ ያሉት የመኖር ትርጉም ሕሊናውን ሰቅዞ ይይዛል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ራሱን የመሆን ችሎታ አለው፡፡ ችሎታው ግን የማሰብ ሃይሉን የሚጠይቅ ነው፤ በሃሳብ መውጣት መውረድን ይሻል፡፡

ከራስ የተፋታ ዕውቀት የትም አያደርስም፡፡ ስለሌሎች አውቀህ ስለራስህ ባታውቅ ጎዶሎ ትሆናለህ እንጂ አትራፊ አትሆንም፡፡ ራሳቸውን የሚያውቁ መሪዎች፣ ራሳቸውን የሚገነዘቡ ምሁሮች፣ ስለራሳቸው በቂ ዕውቀት ያላቸው ባለሞያዎች ለሐገራችን ያስፈልጓታል፡፡ በየትኛውም ዘርፍ ራሳቸውንም ሆነ ዘርፉን በበቂ ሁኔታ የሚያውቁ ሰዎች በራሳቸውም ሆነ በሐገራቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ፡፡ ራሱን መምራት የማይችል ሰው ቀበሌ እመራለሁ ቢል አይሳካለትምና፡፡

ራስን ስለመሆን ጥንታዊ ፈላስፋዎች ብዙ ብለዋል፡፡ በሃሳባቸው ወትውተውናል፡፡ ዛሬ The Collector በተባለ ድረገፅ የወጣ አንድ ፅሁፍ ቀልቤን ስቦታል፡፡ ፀሐፊዋ ቪክቶሪያ ሰስ (Viktoriya Sus) የምትባል ሲሆን የነፍሷን ረሃብ የምታስታግሰው የፍልስፍና ሃሳቦችን በመተንተን ነው፡፡ በተለይ የፈረንሳዊውን ፈላስፋ ሳርትራንና የጀርመናዊን ፈላስፋ ማርቲን ሄድገር ስራዎችን በማቀንቀን ትታወቃለች፡፡ ይቺ ሴት በዚሁ ድረገፅ ‹‹አምስት ታዋቂ የፍልስፍና ጥቅሶች ሕይወትህን ሊለውጡ ይችላሉ (5 Famous philosophy quotes that can change your life)›› በሚል ርዕስ ሃሳቦቹን አንድበአንድ ተንትናለች፡፡ ትንታኔዎቿን በአጭሩ አቅርቤዋለሁና ተከተለኝ፡-

1. በአንደኛነት ያስቀመጠችው የሶቅራጦስን ጥቅስ ነው፡፡ ሶቅራጦስ ‹‹ያልተመረመረ ሕይወት ዋጋ የለውም (The unexamined life is not worth living)›› የሚለው ሲሆን ይሄም ሃሳባችን ጥራት እንዲኖረውና ሕይወታችን ትርጉም አልባ እንዳይሆን ያደርጋል ትለናለች፡፡ ራሱን የሚጠይቅ፣ ስሜቱን የሚገመግም፤ የዕውቀቱን ልክነት የሚፈትሽ ሰው የሚኖረው ሃሳብ የጠራ ይሆናል፡፡ የጠራ ሃሳብ የጠራ ዕውቀት፤ የጠራ ዕውቀት የጠራ ተግባር፤ የጠራ ተግባር ደግሞ የጠራ ሕይወትን ያጎናጽፋል፡፡

2. በሁለተኝነት ያስቀመጠችው ደግሞ የ89 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑትን አስራ አራተኛው የቲቤታውያን ቡድሂዝም መንፈሳዊ መሪ ቴንዛይን ግያትሶ (Tenzin Gyatso) የተባሉትን የዳላይ ላማ (Dalai Lama) አባባል ነው፡፡ እኚህ ዳላይ ላማ ‹‹ደስታ ተዘጋጅቶ የሚጠብቀን ነገር አይደለም፡፡ ደስታ ከራሳችን ተግባር የሚገኝ ነው፡፡ (Happiness is not something ready made. It comes from your own actions)›› ይላሉ፡፡ ደስታ የራሳችን የአስተሳሰባችን ውጤት እንጂ በውጫዊ ነገር የምናመጣው አይደለም ማለታቸው ነው፡፡ ተግባራችን፣ አመለካከታችን፣ ዝንባሌያችን የደስታችንን ሁኔታ ይወስናሉ፡፡ ቁሳዊ ነገር ስላሟላን ደስታችን ይሟላል ማለት አይደለም፡፡ በቅንጡ ቤት ውስጥ ቅንጡ አስተሳሰብ ከሌለ ቤቱ በራሱ የሚፈጥረው ደስታ የለም፡፡ ተደሳቹም ሆነ አስደሳቹ ነገር ከውስጣችን የሚፈልቅ ነውና፡፡

3. ሶስተኛው አባባል የፍሬድሪክ ኒቼ አባባል ነው፡፡ ኒቼ ‹‹የማይገድለኝ መከራ ሁሉ ያጠነክረኛል (What doesnot kill me makes me stronger)›› ያለው ነው፡፡ ፈተና የሰውን ኑሮውን ብቻ ሳይሆን የማሰብ አቅሙን ይፈትናል፡፡ በፈተና የተጨናነቀ አዕምሮ ራሱን ነፃ የሚያወጣበት መላ አያጣም፡፡ ፈተናዎች መልካም አጋጣሚዎችን እንደሚፈጥሩ፤ ችግሮች አዲስ ዕድል እንደሚያመጡ መከራቸውን ተሻግረው ስኬታማ የሆኑ ሰዎች ምስክሮች ናቸው፡፡ ፈተናን እንደመልካም አጋጣሚ ለመጠቀም አዕምሮን ክፍት አድርጎ መጠበቅ ፈታኝ ሁኔታውን ፊት ለፊት ተጋፍጠን እንድናልፈው ያደርጋል፡፡ አንድን ችግር ትልቅም ትንሽም የሚያደርገው አስተሳሰባችን ነውና፡፡

4. አራተኛው የዘመናዊው ፍልስፍና አባት ተብሎ የሚጠቀሰው የሬን ዴስካርት አባባል ነው፡፡ አባባሉም ‹‹መኖሬን የማውቀው በማሰቤ ነው (I think, therefore I am)›› የሚለው ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ዴስካርት ህልውናዬ ማሰቢያዬ ውስጥ ነው ያለው እያለን ነው፡፡ አንድ ሰው መመርመር፣ መጠራጠር፣ መጠየቅ ወይም ማሰብ ከቻለ እየኖረ ነው ማለት ነው ማለቱ ነው፡፡ ይሄም ራሱን የማይጠይቅ፣ ህይወቱን የማይመረምር፣ ተፈጥሮውን የማይገነዘብ፣ ነገሮችን ሁሉ የማይፈትሽ የእውነት እየኖረ አይደለም እንደማለት ነው፡፡ ማሰቢያህን ካልተጠቀምክበት መኖርህ ትርጉም የለውምና፡፡

5. አምስተኛውና የመጨረሻው የሆነው አባባል ደግሞ የሄራክሊተስ አባባል ነው፡፡ አባባሉ ‹‹ከለውጥ በስተቀር ምንም ቋሚ ነገር የለም (There is nothing permanent except change)›› የሚል ነው፡፡ ሔራክሊተስ በዚህ አባባሉ በዋናነት ሰዎች በህይወታቸው የሚያጋጥማቸው ውጣውረድ፣ ፈተና፣ መከራ፣ ጭንቀት አላፊ ነው፡፡ ቋሚ መከራ የለም፡፡ ወደድንም ጠላንም በለውጥ ባቡር ውስጥ ስላለን ሁሉም ነገር በጊዜው ይለወጣል፡፡ በርግጥ አንዳንድ ለውጥ የግዳጅ ለውጥ ነው፡፡ እኛ ሳንለውጠው በራሱ ጊዜ የሚለወጥ፡፡ ብልህ ሰው ግን የግዳጅ ለውጥ አይጠብቅም፤ ቀድሞ እሱ ተለውጦ ይጠብቀዋል፡፡ ዘመኑን ዋጅቶ መጠበቅ የግዳጅ ለውጥ ሳይመጣ በፈቃድ መለወጥ መቻል ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ…. የራሱ አሻራ፣ የራሱ ምልክት፣ የራሱ መለያ ያለው የሆነ ሰው ሁን፡፡ ዳናህ ልብህን እንጂ የሌሎችን ኮቴ የሚከተል አይሁን፡፡ ማንንም አትሁን፤ ምንምም አትሁን፡፡ የተፈጠርከው ለዓላማ ነውና ዓላማህን ፈልገህ ራስህ ሁን፡፡ ማሰቢያህ ነፍስህ ነው፡፡ ሃሳብህ እስትንፋስህ ነው፡፡ በማሰቢያህ እያሰብክ በሃሳብህ ካልተነፈስክ የምር እየኖርክ አይደለም ማለት ነው፡፡ ማሰቢያህ አንተነትህን እንዲጠይቅ፤ ዓለሙን እንዲመረምር፣ አካሄድህን እንዲገመግም፣ ስሜትህን እንዲያጠና ካላለማመድከው ቆሞ የሚሄድ ስጋ ብቻ ነው የምትሆነው፡፡ ራስህን ሁን ማለት ግን ስለሌሎች አይመለከትህም ማለት አይደለም፡፡ ከሌሎች ጋር ስትደባለቅ ራስህን ሆነህ ይሁን፡፡ ውጫዊ ነገር ስሜት አይስጥህ እያልኩኝ አይደለም፡፡ የሚመለከትህን ለይ፡፡ ማህበራዊ ተፈጥሮ አለህና ሐገራዊ ጉዳይ፣ ሃይማኖታዊ ጉዳይ፣ ፖለቲካዊ ጉዳይ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ፣ ተፈጥሯዊ ጉዳይ ሁሉ ይመለከትሃልና አስፈላጊ ነኝ ብለህ በምታምንበት ቦታ ሁሉ ተሳታፊ ሁን፡፡ ራስህን ሁን ማለት፤ የሆነ ሰው ሁን ማለት; በርህን ዘግተህ ከእውነታው ሽሽ ማለቴ አይደለም፡፡ አንተነትህን ሳትጥል በራስህ ቀለም ሁሉንም እንደየቦታው ተግብረው ማለቴ ነው፡፡