Últimas Postagens de ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖 (@bookshelf13) no Telegram

Postagens do Canal ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖

ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖
"ስለመጻሕፍት ከመጻሕፍት መንደር እንዘምራለን!"
18,903 Inscritos
2,716 Fotos
24 Vídeos
Última Atualização 27.02.2025 06:07

Canais Semelhantes

Dr. Eyob Mamo
79,375 Inscritos
ETHIO BOOKS PDF
20,046 Inscritos

O conteúdo mais recente compartilhado por ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖 no Telegram


ቸር ድል!

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!

____
© እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ ጥር ፲፱ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.

ከሦስት እስከ አምስት ዓመቷ ድረስ በራስ ተነሳሽነት የመሥራት አልያም በተቃራኒው የጥፋተኝነት ስሜትን የምታዳብርበት ወቅት ነው። የብላቴና ዘመን ዕቅዶቿን ለማሳካት በምታደርገው መውተርተር የሚሰጣት ምላሽ ይሄንን ስሜት እንዲገነባ ያደርጋል። እዚህ ጋር ሎዛ የምትባለው ገጸባሕርይ ከልጅነቷ ጀምሮ መሥራት የምትፈልገውን ነገር ያለማንም ከልካይ ትከውን እንደ ነበር በታሪኳ መሐል ተሰንጎ እናገኛለን። ሎዛ ከጥፋተኝነት ስሜት የራቀ ማንነት የገነባችው በአባቷ ምክንያት ነው። በራስ ተነሳሽነት አንዳች ነገር ስትጀምር ከአባቷ ዘንድ ቅቡልነት ታገኝ ስለነበር ከአደገች በኋላም ይሄን የማኅበራዊ ልቦናዊ ጡብ የምናገኘው በአዎንታዊው ኩርባ ነው።

ከስድስት እስከ ዐሥራ አንድ ዓመቷ ደግሞ የተወዳዳሪነት ስሜትን ወይም የበታችነት ስሜትን በማንነቷ ላይ የሚገነባበት ወቅት ነው። እዚህ ደረጃ ላይ መምህራን ወሳኝ ናቸው። ማምሻ የሞት ሞቷን እስከ ዘጠነኛ ክፍል ብትጓዝም ቀለም ግን ፈጽሞ ሊዘልቃት አልቻለም። በሠራችው ሥራ የበላይነት ስሜትን እንዳትጎናጸፍ ተደርጋ ይኾን? አብርሽ የተባለው ተራኪው ገጸባሕርይ ስለማምሻ ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዲህ ይላል፡- “በፌዝ - ከእኩዮቿ ጋር እኩል የማትቆም - በልጅነቷ የማኅበረሰቡ ግፍ ከብዷት የጎበጠች ወጣት ተፈጠረች።” የተወዳዳሪነት ስሜቷን በየቀኑ ማኅበረሰቡ እየቸረቸፈባት እንዴት ቀና ያለች ሴት ትፈጠር?

ከ12 - 18 ዓመቷ ደግሞ ጥንቅቅቀ ያለ ማንነት የምትገነባበት አልያም ግራ መጋባት የሚሠለጥንባት ወቅት ሲኾኑ ራስን ለመቻል፣ ከጥገኘነት ለመላቀቅ በሚሞክሩት ሙከራ በሚሰጣቸው ምላሽ ላይ ይመሠረታል። ትምህርት አልሆን ሲላት ከድር የተባለው ጫታም ደላላ ጋር ሄዳ፣ ሻይ ቤት እንዲስያስቀጥራት ስትነግረው፣ “ማምሻ … በዚህ ፊት አስተናጋጅነት…” ብሎ ተዘባበተባት። ቆየት ብላ የቦኖ ውኃ ቀጂነት ሥራ አገኘች። ግን እምብዛም አልቆየች። “ውኃ አታፍስሱ!” ብትላቸው እያሸሞሩባት ቁጡ አደረጓት። አንድ ቀን አንዷ ላይ ተከምራባት እልኋን ተወጣችባትና ከሥራ ተባረረች። ቤቷ ተከተተች። ጥንቅቅ ያለ ማንነት በሚገነባበት ዘመኗ የግራ መጋባት አስኬማ ደፍታ መነነች።

እስኪ ደግሞ ለንጽጽር ሎዛ ጋር እንሂድ። ሎዛ በአባቷ ምክንያት የተወዳዳሪነት ስሜቷ ላቅ ያለ ስለኾነ ባለጽኑ ማንነት ሆና እናገኛታለን። በዐሥራ-ቤቴ ዘመኗ ዩኒቨርስቲ ስትገባ የተፈጠረው ክስተት ለዚህ ትልቅ አስረጅ ነው። “እብደትን አትማሪያትም!” በሚል ንግግር እናቷን ጨምሮ ከሁሉም ሰው ዘንድ ተቃውሞ ገጠማት። “ሁሉም ተቃውመውኝ እኔ ብቻ ልክ ልኾን አልችልም” የሚል ግራ መጋባት ውስጥ ሳትገባ በጽኑ አቋም የመረጠችውን የፍልስፍና ትምህርት እንደተማረች ከታሪኩ ውስጥ እናገኛለን። የአባቷ ምላሽም እሷን የሚደግፍ ስለኾነ ከመደናበር (Role Confusion) ተሻግራ ወደ ሌላኛው እርከን ትሄዳለች። ወደ መወዳጀት መቻል። በአንጻሩ ግን ማምሻ ለዚህ አልታደለችም። ሎዛ በአባቷ ዘንድ ያላት ቅቡልነት ማምሻን ታህል በማኅበረሰቡ የተገፋችን ሴት ወደ መቀበል አሳደጋት። ግፋ ሲልም ሚዜዋ እስከማድረግ። ከዳግም ጋር ደግሞ ትዳር እስከ መመሥረት።

ከ19 -40 ባለው ዕድሜ ውስጥ የመቀራረብ ስሜት ወይም ራስን የመነጠል ስሜት የሚደረጅበት ነው። ከቅርብ ዘመድ ውጭ ከኾነ ሰዎች ጋር በሚደረግ ዘለቄታ ያለው መስተጋብር ውስጥ በሚኖረው የመሳካት ዕድል የሚወሰን ነገር ነው። ማምሻ የመቀራረብ ስሜት ለመገንባት ዕድሉን አላገኘችም። ከሁሉ ወጥታ፣ ራሷን ነጥላ ቤቷ ተከተተች። ወላጅ እናቷ የሰው ቤት ሠርታ በምታመጣው ፍራንክ የሰቀቀን ኑሮውን ተያያዘችው። ነገር ግን ባቀረቀረችበት ኪሮሽና ክር አንስታ ውብ ዳንቴሎችን፣ አልጋ ልብሶችን፣ የመጋረጃዎችን ጥልፍ ማምረት ጀመረች። ማኅበረሰቡ የማምሻን የእጅ ሥራ ውጤቶች ይሸምት ጀመር። የማምሻን አስቀያሚነት ውብ የእጅ ሥራዋ የዋጠው መሰለ። እናቷን በየሰው ቤት ከመንከራተት አዳነች። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ዘመናዊ የጥልፍ መኪናዎች መጡና የማምሻን እጅ ሰበሩ። ዳግም ወደ ማቀርቀሩ ተመለሰች። እናቷም ወደ ቀደመ ሥራዋ ተመለሰች። ማምሻ በቀቢጸ ተስፋ ዛጎል ተከተተች። እንግዲህ ሎዛ ከዚህ ሁሉ አሉታዊ የማኅበራዊ ልቦናዊ ማጥ ውስጥ ነው ማምሻን መንጭቃ እንድትወጣ የረዳቻት።

በዚህ ታሪክ ውስጥ የኤሪክሰንን ሰባተኛ እና ስምንተኛ ደረጃ እርከኖችን ለማተት ስለሚቸግር በዚህ እናበቃለን።

የዳሰሳው አቅራቢ - © ቢኒያም አቡራ is an associate editor at © Think Ethiopia ([email protected])

ጥር 13፣ 2017 ዓ.ም

ከዕለታት የማምሻ ቀን

የመጽሐፉ ርዕስ - ከዕለታት ግማሽ ቀን
ዘውግ - የአጫጭር ልቦለድ መድብል
ደራሲ - አሌክስ አብርሃም
የኅትመት ዘመን - 2013
Rating : 8.6

የማምሻ ፉንግና

የማምሻን እያንዳንዱን የሰውነት ክፍሏ ምን ያህል አስቀያሚ እንደ ኾነ ከመግለጽ ይልቅ፥ በማኅበረሰቡ የፉንግና መድሎት ላይ ያውላታል። ማኅበረሰቡ ባወጣው የቁንጅና መስፈርት ውስጥ ይገልጻታል። ዓይኗ፥ ጥርሷ፥ ከንፈሯ ከማለት ይልቅ በሰዎች አንደበት ውስጥ ያለውን አተያይ በመጠቀም ምስሏን ይከስታል። ለአብነትም፡- ዓይን የማይለምደው መልከ ጥፉነት … በቀለኛ አጋንንት በአጉሊ መነጽር እየተመለከተ፥ ትንሽ ሰውን ሊስበው ይችላል ብሎ የጠረጠረውን ሁሉ እየለቀመ ያፈራረሰ ነው የሚመስለው … እኔ ነኝ ያለ ደራሲ ቀርቶ ፎቶ አንሺ ራሱ በበቂ ሁኔታ ማሳየት የሚሳነው መልክ … ይሄ ቸብ ያደረገህ እጅ የማምሻ ቢኾን ኖሮ መፍለጫ እንዳረፈበት ጉቶ ወለል ላይ ትበታተን ነበር … እና መሰል አገላለጾችን በመጠቀም የማምሻን ፉንግና በእዝነ ልቦናችን እንዲከሰት ያደርጋል። ግሩም ዝየዳ ነው።

“ዓለም ፈውሷን እንድትቀበል የሎዛ ዓይነት እብዶች ሳያስፈልጓት አይቀርም!”
አንድ እጭ እንቁላል ውስጥ እያለ ከባድ ጊዜን ያሳልፋል። እንቁላሉን ሰብሮ ለመውጣት ይታገላል። እንቁላሉን ሰብሮ ለመውጣት በሚያደርገው ተጋድሎ ጡንቻዎቹ እየፈረጠሙ ይሄዳሉ። እንቁላሉን ራሱ ሰብሮ ሲወጣ የፈረጠመ ጡንቻ ስለሚኖረው ክንፎቹ ሳይዝሉ ለረዥም ጊዜ ይበራል። ነገር ግን እጩ በእንቁላል ውስጥ ኾኖ ከሚያደርገው መፍጨርጨር የተነሳ አንድ ሰው አዝኖለት እንቁላሉን ቢሰብረው እጩ ተጎጂ ነው። ከተሰበረለት እንቁላል የወጣ እጭ ጥቂት እንደ በረረ ይፈጠፈጣል። ምክንያቱም እንቁላሉን ለመስበር ጥረት በማድረግ ሂደት ውስጥ ያገኝ የነበረውን ጥንካሬን አይታደልምና። ከዚህም የተነሳ ከጥቂት ምዕራፍ በቀር መብረር ይሳነዋል። ይህ የገባት ሎዛ የማምሻን እንቁላል አትሰብራላትም፤ ለዚያም ነው ማምሻ በቀላሉ ክንፎቿ ያልዛሉት።

መኪና በሰዎች ኃይል ሲገፋ ጥቂት ሄዶ ይቆማል። ከራሱ ከሞተሩ ኃይል ከሆነ ግን አያሌ መንገድ ይጓዛል። የሰው ግፊት የሚያስፈልገው ሞተሩን መንጭቆ ለማስነሳት ነው። ሎዛ የማምሻ ሞተር እንዲነሳ ብቻ ነው የገፋችው። በዚህ ዐውድ ሴቶችን የማጎልበት (women empowerment) ተኮር የኾኑ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ለሴቶች ሞተር መኾን እንደ ማይችሉ ጥቁምታ ሰጪ ነው። አነቃቂ ንግግርም (motivational speech) የመጨረሻ ግብራቸው መኪናውን መግፋት ብቻ መኾኑን ያሳያል።

ሎዛ የማምሻ ሞተር መንጭቆ እንዲነሳ ጥቂት ግፊት አድርጋለች ማለት የሎዛን ግብር ማሳነስ አይደለም። “አገሩ የበጎች ነው። ግን የበጎች ታሪክ ቦታ የለውም። በጎች ራሱ የሚተርኩት የአንበሶችን የጀግንነት ጀብዱ ነውግሩም ዝየዳ ነው። ምናልባት ታሪኩ የበጎችን ስም ካነሳ፤ በአንበሶች እንዴት እንደተበሉ ከመተረክ _ አያልፍም። የበግ ቆዳ የለበሱ አንበሶች ጠላታቸው የለበሱት ቆዳቸው ነው፤ ስለዚህ ይህን ቆዳ እንዲገፉትና ታሪካቸው እንዲጻፍ ትንሽ መርዳት አለብን። በሚል መነሻ ነው ማምሻን የምታግዛት። ሎዛ “ብዙ አይደለም…ትንሽ!” ብትልም ቅሉ ነገሩ ቀሊል አይደለም። ሲጀመር ሎዛ ለማምሻ ያደረገችላትን ነገር ለማድረግ ሎዛነትን ይጠይቃል። የሎዛን እብደት ይሻል።

ሎዛ ባዶ ቀረርቶ አይደለም ለማምሻ የለገሰችው። "ትችያለሽ!" የሚል ባዶ የማነቃቂያ የጅምናስቲክ ትርዒት አይደለም ያቀረበችላት። ማኅበረሰቡ በማምሻ የተጠለፉ ጥልፎችን ንቆ በዘመናዊ ማሽኖች የተፈበረኩ አልባሳትን ሲመርጥ፥ የማምሻን የእጅ ሥራ የለበሰችው ብቸኛ ሴት ሎዛ አይደለች? አብርሽ በእምቢታ የተወውን ትኩስ እንጀራ በመመገብ አይደል ሙያ እንዳላት በስውር የምትነግራት? ማምሻን “ለሰርግ ታዳሚነት ብቁ አይደለችም!” ብሎ በሚያምን ማኅበረሰብ ውስጥ፥ አንደኛ ሚዜ አድርጋ ለመሾም መሞከሯ ብቻውን ማምሻን እንደገና የመውለድ ያህል አይደለምን? … ሕጻናትን ለማስፈራራት “ማምሻን እንዳልጠራልህ”! የምትባለዋን ሴት፥ ለአንደኛ ሚዜነት እጩ ማድረግ ዕውን ቀላል ውለታ ነው? … በሰርጓ ቀን በጥበብና በወርቅ የተንቆጠቆጡ አክስቶቿን ረግጣ፥ ማምሻን ብቻ በማቀፍ የመፈለግ ስሜቷ ላይ ትንሳዔ አልዘራችባትም? ይሄ “አንቺ ተፈላጊ ሴት ነሽ” ከማለት የበለጠ መልዕክት አያስተላልፍም? ዱዱሻ የተባለች ሕጻን - አረንጓዴ እና ጥቁር ቀለም በመጠቀም በሳለችው ስዕል ላይ፣ “ማምሻ ሕጻኑን ልትበላ” በማለት የጻፈችው ስዕል - ከፒካሶ ስእል በላይ ቅርስ ሆኖ የሰፈሩ መሳቂያ የነበረችን እንስት፣ በሰርግ ቀን ሄዶ ማቀፍ ትርጉሙ ምንድነው? … “የምትናገሪበት አፍ አለሽ!” ከማለት ይልቅ ጆሮዋን በመስጠት አይደል የፈወሰቻት? ለዚያም አይደል ወደ ኋላ ላይ “አባትሽ ጋር ከሚሠሩ ሠራተኞች በምን አንሳለሁ ሎዛ?” የሚል አብርሆታዊ መጠይቅ ማምሻ ያቀረበችው? ሎዛ በጆሮዋ የማምሻን ዲዳነት ፈወሰችው ማለት ይህ አይደል? … ማኅበረሰቡ ሰገራ እንደ ነካ እንጨት ለወረወራት ሴት ማን ጆሮ ያውሳል? … ከወንዶች እኩል እንደምትሠራ እምነት እንዳላት ለአባቷ ነግራ ሥራ በማስቀጠር አይደለ “እምነት የሚጣልብሽ ሴት ነሽ” የሚል መልዕክት ያሰተላለፈችላት? ባዶ ሜዳ “አምንሻለሁ” ከማለት አይሻልምን? የማምሻ አባት “ወንድ ልጅ እስኪገኝ መቆያ ትሁን” ሲል “ማምሻ ቢኾነኝ” የሚል አሉታዊ ትርጓሜ ያዘለ ስያሜ በሰጣት ሴት የገዛ ልጅን መሰየም ትርጉሙ ምንድነው? ስም ውስጥ ንግርት አለ ብሎ በሚያምን ማኅበረሰብ ሎዛ የልጇን ስም ማምሻ ብላ በመሰየም አይደል የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ የምትቃወምላት? የልጇን ስም ማምሻ ዳግም በማለት አይደል አሉታዊ ስያሜ፥ ከእርምጃ የሚገታ እግረ ሙቅ እንዳልኾነ የምትነግራት?

ሎዛ - የለውዝ ዛፍ ማለትስ አይደል? … እግዚአብሔር ነብዩ ኤርሚያስን “ምን ታያለህ?” ሲለው፣ “የለውዝ በትር አያለሁ!” በማለቱም አይደል “መልካም አይተሃል!” የተባለው? ማምሻንም ፈጣሪ “ምን ታያለሽ?” ቢላት፣ “ሎዛን አያለሁ!” የምትል ይመስለኛል። “መልካም አይተሻል!” እንደሚላት ጥርጥር የለኝም።

የዐምድነሽ ጀልባ፥ የማኅበረሰቡ ወጀብ፥ የሎዛ መቅዘፊያ እና የዳኒ ደሴት
የማምሻ ሞተር የተነሳው በትብብር ክንድ ነው። ወላጅ እናቷ ዐምድነሽ በየሰው ቤት ተንከራተው አሳደጓት። የሎዛ እብዳዊ መቅዘፊያ ለማምሻ የማኅበረሰቡን ወጀብ የምትጋፈጥበት መሣሪያ ሆነላት። ዳኒ ደግሞ ሙያን አስተምሯት፥ ትዳርን ያህል ጎጆ ቀልሶ ልጅን ያህል ስጦታ አስታቀፋት። የሕጻን ልጅ ውበት በልጅነቱ ውስጥ፥ የወጣት ውበት በአካሉ ላይ፥ የጎልማሳ ውበት በግርማ ሞገሱ እና የሽማግሌ ውበት በልምድና በእውቀቱ መኾኑ የገባው ዳኒ፥ ማምሻን ለማግባት አንዳች አላቅማም ነበር። ዳኒ ነው አናፂነት ያሰተማራት። እንጋባ ሲላት የቀልዱን ነበር የመሰላት። አንቺን የምትመስል ልጅ ነው የምፈልገው ሲል ግራ ገብቷት ነበር።

ቅሪት ስትኾን የጨነቃት እንደ ሴት የምጥ ጉዳይ ሳይኾን የልጇ መልክ ነበር። ገና ተወልዳ እንዳሳቀፏት የልጇን ጾታ ለማወቅ አልጓጓችም። የልጇ ቆዳ በመፍካቱ እና ራሷን ባለመድገሟ ነበር በሐሴት የተዋጠቸችው። ለዚያም ነው ልጇን አቅፋ በደስታ አለቀሰች። እውን ራስን አለመድገም ያስደስታል? … በማኅበረሰቡ ቅቡል የኾነ መልክ መውለድ ማኅበረሰቡን ከመውለድ ይተናነሳል? … ይሄ ተረክ በየቀዬያችን ያሉ ማምሻዎች ላይ ምን ያህል የወል ጥቃት (collective violence) እንዳደረስን ማሳያ አይደለምን? …

የደስታዋ ምንጭ “ልጅሽ ቁርጥ አባቷን” ሲሉ መኾን ነበረበት?

ማምሻ በዐምድነሽ ጀልባ ላይ ተቆናጥጣ፣ ማኅበረሰብ የተባለ ማዕበል እያፍገመገማት፣ በሎዛ መቅዘፊያ ከዳኒ ደሴት የደረሰች ብርቱ ተጓዥ ናት። የተረጋጋ ሐይቅ ላይ መቅዘፍ የለመደ ሰው ጥሩ የጀልባ ቀዛፊ አይሆንም፤ በማዕበል የሚናወጥ ቀጠና ጋር ሲደርስ ይዋጣልና። ማምሻ ከልጅነት እስከ ዕውቀት በማኅበረሰብ ማሰሮ ተንጣ ከአናታቸው ላይ የወጣች ንጹሕ ቅቤ ናት። ማምሻ ኮብልሎ የሸሻት አባቷ አቶ ቢኾነኝን የምታስከነዳ ጽኑ ናት። ለሚዜነት አትመጥኚም ባዮቹን የሎዛ እናት፣ አባት፣ ፍኖትን፣ አብርሽን … መሳሳታቸውን የሚያሳይ ሕያው ዶሴ ናት። ውኃ እየደፉ ለውጥን፣ ሕይወትን፣ ንጽሕናን የገፉ ማኅበረሰብን ትምህርት የምትሰጥ የምትገለጥ መጽሐፍ ናት።

የሬሳ ሳጥን ሻጯ ማምሻ

የሬሳ ሳጥን ሻጭ በቀቢጸ-ተስፋ የተመላ፣ በሌሎች ጉዳት ውስጥ ትርፍ የሚያካብት፣ ሙያዊ የውዝግብ አጣብቂኝ (ethical dilemma) የሌለበት፥ ግብረገባዊ ውድቀት እንዳስከተለ ሰው ይታያል። በዚህ አጭር ልቦለድ መቋጫ ላይ ማምሻ የሬሳ ሣጥን ሻጭ ኾና ብቅ ትላለች። አብርሽ ለተሰኘው ገጸባሕርይ “ለምን እንደኾነ አላውቅም ግን የሬሳ ሣጥን ስሠራ ደስ ይለኛል” ትላለች። እሷ ተወልዳ ያደገችበት ሰፈር ላይ ያሉ ሰዎች ሲሞቱ የሚቀበሩት እሷ በሠራችው የሬሳ ሣጥን ውስጥ ነው። እውን ማምሻ በሌሎች መጎዳት ውስጥ ትርፍ ማጋበሷ ነው ያስደሰታት?

በኔ አተያይ ማምሻ በፌዝ ቢለዋ የተለተሏት ሐሳቦችን፣ የልጅ ማስፈራሪያ ያደረጋትን አመለካከት፣ የአትችይም መፈክር የያዘውን ሙት ሐሳባቸው የሚቀበርበትን የሬሳ ሣጥን የምታዘጋጅ አናፂ ናት። የማኅበረሰቡን የወል ጥቃት (collective violence) በሷ የእጅ ሥራ እየተቀበረ መኾኑንስ አይጠቁመንም? ታዲያ በዚህ ያልተደሰተች በምን ትደሰት? በሬሣ ሣጥኑ የሚቀበሩት የተቃወሟት፣ ያንኳሰሷት፣ አትችይም ያሏት ሰዎች ሳይኾኑ ሐሳቦቻቸው ናቸው። ሣጥኑን የምትሠራበት መዶሻ እጀታው ወርቃማ በቀል ቢመስልም ቅሉ፥ ቀጣዮቹ ማምሻዎች እንዳይጎዱ መንገዱ ላይ ያሉ ቁሙዱዎችን በጨፈቃ እንደ መጥረግ ያለ ትልም ይነበብበታል፤ ባይ ነኝ።

ማምሻ በገዛ እጆቿ በሠራችው የሬሳ ሣጥን የነገረ - ሴትን አተያይ ለመቅበር ታትራለች። አወዛጋቢው ብሪታኒያዊው ዲ ኤች ላውረንስ ስለ ሴቶች እንዲህ ይለናል፦ "የሴቶች ዋነኛ ችግር ወንዶች ስለሴቶች የሚኖራቸውን ጽንሰ ሐሳብ አሟልተው ለመገኘት መጣራቸው ነው" ብዙ ወንዶች የሚፈልጓትን አይነት ሴት መስለው። ኾነው። ማምሻ በወንዶች ዘንድ ያለውን የሴትነት መስፈርት አታሟላም። በማጌጫ እና በዱቄት ተለብጣ ከመስፈርቱ ልትገባ ስትሞክርም አናይም። መስፈርቱ ግን ምን ይኾን? … ሎዛ መረር ባለው አንደበቷ የምትጠቁመን ይኾን? … "እግር የተፈጠረበት የመጀመሪያ ዓላማው መራመድ ነው፤ (ወዳሰበችበት) ከመራመድ በላይ የአረማመዷን እና የእግሯን ውበት እንድታስብ ስትስበከ ኑራለች። … እጅ የተፈጠረበት የመጀመሪያ ዓላማው መሥራት ነው። … ብዙ የፋሽን እና ዘመናዊውን የውበት ሚዛን የሚደፉ 'ዘመናዊ' ሴቶች፣እጃቸው ከሚበላሽ ስማቸውም ሕይወታቸውም ቢበላሽ እና እጃቸው እንደለሰለሰ ቢኖር ይመርጣሉ። … ለዚያ ነው በሥራ ስለደደረ የሴት መዳፍ፣ ዘፋኙም መዝፈን፣ ገጣሚውም መግጠም የማይወደው። … በልስላሴ ሳይሆን በንጽሕናና ራስን ችሎ በመቆም እንጨባበጥ ከተባለ ማንናት ደፍራ እጇን የምትዘረጋ?! … ማምሻ ቆንጆ አይደለችም። ዕጣ ፋንታዋ ዓይንና ጥርሷ ላይ ሳይሆን፣ እጆቿ ላይ እንዳለ ግን ተገልጦላታል። ወንድ በእግሮቿ መሃል ካላለፈ የሚያልፍላት የማይመስላት ሴት አይደለችም።” ትለናለች። ማምሻ በገዛ እጆቿ በሠራችው የሬሳ ሣጥን የነገረ - ሴትን አተያይ ቀብረዋለች ለማለት ምን ይጎድለናል ታዲያ?

የሎዛ እናት ልክ አደፍርስ ላይ እንዳለችው ወ/ሮ አሰጋሽ ሰውን በመደባዊ አተያይ የመመልከት እርሾ አላቸው። ወይዘሮ አሰጋሽ ለአደፍርስ እንዲህ ይሉትም የለ? “ከሰውም ሰው አለው፤ “ከእንጨት መርጦ ለታቦት፤ ከሰው መርጦ ለሹመት” ሲባል አልሰማህም የኔ ልጅ? … አሁን ለምሳሌ አሽከሮቼን ገና ለገና በዝጌር አምሳል ተፈጥረዋል ብዬ ከኔ ጋር እኩል ናቸው ልል ነው? የለም የኔ ልጅ!” ይላሉ ወይዘሮ አሰጋሽ። አርስቶትልም "እኔ ቁጭ ብዬ እንዳስብ ምግብ የሚያበስልልኝ አካል ያስፈልጋል" የሚል መደባዊ አስተሳሰብ ያራምድም የለ? የሎዛም እናት “ታዲያ (ማምሻ) ሰው የኾነች እንደኾነስ? … እግዜር ሲፈጥረን መቸም ቦታ ቦታ አዘጋጅቶ ነው!” ይሉም የለ? ማምሻ እንዲህ ያለውንም አተያይ ሲቀበር እንደ ምታይ በማሰብ ነው የሬሳ ሣጥን ስትሠራ በሐሤት የምትሞላው፤ በኔ አመለካከት።

ማኅበረ-ልቦናዊ ዕድገት በማምሻ ታሪክ ውስጥ

ውልደቱ ጀርመን ቢኾንም በአሜሪካዊ ዜግነት የሚታወቀው ኤሪክ ኤች ኤሪክሰን Identity and the Life Cycle በተሰኘ መጽሐፉ፥ ማኅበረ-ልቦናዊ ዕድገትን በዕድሜ በዕድሜ ከፋፍሎ በስምንት አዎንታዊ እና አሉታዊ ስፍን ያስቀምጣል። "ማምሻ" የተሰኘው የአሌክስ አብርሃም ድርሰት ረዥም ልቦለድ ቢኾን ኖሮ፥ ማምሻን በኤሪክ ኤሪክሰን ትወራ ውስጥ ለስምንቱም ደረጃ የሚኾን ቅንጣት በየአንዳንድ የታሪኳ አንጓ ውስጥ እናገኝ ነበር። "ማምሻ" የአጭር ልቦለድ ዘውግ ስለሆነ ተረኩ እሚነጉደው በጥድፊያ ጎማ ነው። መኾንም አለበት። እኛም በጥድፊያ የሚመለከተንን ሰበዝ ብቻ በመምዘዝ በመጠኑ እንመልከት።

ከውልደት እስከ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ባሉ ወራት ውስጥ እምነት ወይም ጥርጣሬ የሚሸመንበት ወቅት ነው። ይሄ በወላጆቿ እጅ ላይ ያለ ብዕር ነው። የተወለደችው ልጅ ተጠራጣሪ ወይም አማኝ እንድትኾን፥ ወላጆቿ የሚጽፉላት የአስተዳደግ ድርሰት ወሳኝነት አለው። የማምሻ ወላጆች እንክብካቤ ሰጥተዋታል ወይስ ነፍገዋታል? ወላጆቿ ማምሻ በተባለች ብራና ላይ እምነት ወይስ ጥርጣሬ ነው የከተቡት? አራስ ጥየቃ የሚመጡ ጎረቤቶች ማምሻን ላለመሳም የሚያደርጉት ሽሽት አባቷ እንዲሸሽ መዋጮ አላዋጣም? አራስ ሕጻኗን ማምሻን ለመሳም አንዳንዱ ሲገደድ፥ ዝግንን ብሏቸው ዓይናቸውን ሲጨፍኑ አባቷ አላየም ማለት እንችላለን? ባያይስ አይገባውም? ማምሻ አድጋ አግብታ ወልዳ ባለቤቷ የኾነው ዳኒ “አንድ ቀን እኔና ልጄን ጥሎን ይጠፋ ይኾን” የሚል ሥጋት እንዴት ተሰማት? ይህ የኾነው አባቷ ጋሽ ቢኾነኝ በልጅነቷ እሷንና እናቷን ጥሎ ጠፍቶ ሌላ ቆንጆ ሴት ስላገባ አይደለምን? በጨቅላነቷ የተዘራባት እምነት ሳይኾን ጥርጣሬ ነበር። ለዚህስ ማኅበረሰቡ የአቅሙን አላዋጣም? የወለዳቻት ልጅ ራሷን ባለመምሰሏ ታዲያ ለምን ማምሻ ተደሰተች? ሌላ ልጅ መውለድን የፈራችው ለምንድነው? ድንገት እሷን የምትመስል ልጅ ብትወልድ የእሷን እግር የተለተለው ቁሙዷዊ የማኅበረሰቡ ጉጠት ልጇንም መራመድ እንዳትችል እንዳያደርጋት አይደል? በማምሻ ሰውነት ውስጥ የሚመላለሰው ደም ሳይኾን ጥርጣሬ አይደል?

ከሁለት ዓመቷ እስከ ሦስት ዓመቷ ደግሞ ራስን የመቻል ወይም የኅፍረት ጡብ የሚገነባበት ነው። ነገርን በራስ ለመከወን በምታደርገው መጣጣር የምታገኘው ቅቡልነት ነገርየውን ይበይናል። ማምሻ የአትችይም ጉጠት ከዚሁ ይሆን የጠቀጠቃት?

Title እንስራው
Author አንዱዓለም ተፈራ
Publication Year፳፻፲፩ ዓ.ም
Pages 382
Genre ረጅም ታሪካዊ ልብወለድ
Rating 9.3

እንስራው ረጅም ታሪካዊ ልብወለድ መጽሐፍ ነው። መቼቱ - የት? በዋነኛነት አዘዞ/ ጎንደር ሲሆን መቼ? -ወቅቱ ከአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት እስከ ኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት ይደርሳል።

እንስራው ስምንት ክፍሎችና ሰማንያ ምዕራፎች ያሉት የደጎሰ ጥቅጥቅ መጽሐፍ ነው።
የመጽሐፉ ታሪካዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ስነ ልቡናዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ስነ ልሳናዊ ጥልቀት ለአጭር የንባብ ዳሰሳም ሆነ መጽሐፉን በሚመጥን ደረጃ ሒሳዊ ንባብ ለማካሄድ በመመረቂያ ጽሑፍ ጥናቶች ካልሆነ በቀር ለመጣጥፋዊ ሃያሲ ሥራውን ከባድ አድርጎታል። ይህ ጽሑፍ አጠቃላይ ምልከታ ነው።

የመጽሐፉ አጠቃላይ ምልከታ መጽሐፉን ለማስተዋወቅና በቀጣይነት መጽሀፉ ላይ ለማቀርባቸው ተከታታይ መጣጥፎች ይህ ፍኖተ-መግቢያ ነው። በግል የንባብ ተሞክሮ ሆነ ባለኝ የትምህርት ዝግጅት እንስራው የዘመናችን የፍቅር እስከ መቃብር፣ የአደፍርስ፣ የአዳም ረታ መጻሕፍት ወደረኛ ነው። በልበ ሙሉነት እንስራው ዘመን ተሻጋሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ክላሲክ መጽሐፍ ከሚባሉት ዓይነት መሆኑን እመሰክራለሁ።

ለመጽሐፉ የቋንቋ የስነ ጽሑፋዊ ውበት እና ምጥቀት ከደራሲው ክህሎት በተጨማሪ የስነ ጽሑፍ ምሁሩ አቶ ዘሪሁን አስፋው አርትኦትም ተጨማሪ ግብዓት ሆነውታል።
ከዘሪሁን አስፋው በተጨማሪ በስምና በዝና የምናውቃቸው ኢትዮጵያውያን መጽሐፉን አንብበው አስተያየት ሰጥተዋል። ለምሳሌ እነ ሰሎሞን ዘመነ "እኔ ወድጄዋለሁ"፣ ሰሎሞን አስናቀ፣ ሁሴን ደስታ፣ "ገጾቹ በግእዝ ቁጥር ደምቀው ማየቴ አስደስቶኛል"፣ የታሪክ ፕሮፌሰሩ ኃይሌ ላሬቦ "አንባቢ ደስ እንደሚለው እርግጠኛ ነኝ"፣ መቶ አለቃ አያልሰው ደሴ "እንስራውን" አንብበው ምስክርነታቸውን ለግሰውታል።

መጽሐፉ የሚጀምረው በዘሪሁን አስፋው (የስነ ጽሑፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር) መግቢያ ነው። የዘሪሁን ጽሑፍ ከስነ ጽሑፍ አንጻር መጽሐፉን የገመገመ ጥሩ ሀቲት ነው። ዓይንን ገላጭም ነው፤ አዳጋሚም አይደለም።እንስራው እንደ ታሪካችን እንደ ሕይወታችን ሁሉ ራሮት፣ ብሶት፣ ድቀት ቢበዛበትም እንስራው ተስፋ ፈንጣቂ ነው። መጽሐፉ ሲደምደም የመጨረሻዎቹ ዲስኩሮች "እናም እታለም! ነገ ምን ይሆናል?" ስትባል "ነገማ፣ ነገማ ጸሓይ ትወጣለች።" በማለት ነው መጽሐፉ ሀቲቱን የሚቁዋጨው በአዎንታዊው ተስፋ ነው። ያው በተስፋ የምንኖር ሕዝቦች አይደለን!ሆነም ቀረ ለእንስራው ለዚህ ግዙፍ ክላሲክ መጽሐፍ ያለኝን ፍኖተ መግቢያዬን ከባህል፣ ከታሪክ፣ ከስነ ቋንቋ እና ስነ ጽሑፍ አንጻር ላጋራችሁ።

ከባህል አንጻር

ደራሲ አንዱዓለም ከርዕሳቸው እንስራው ጀምሮ ባህላዊ እሴቶቻችንን አሳይተውናል። በዚህም ተሳክቶላቸዋል።ትውልድ ለትውልድ ማሰብን- ዕውቀትንና ንብረትን በተገኘው መንገድና ዘዴ ሁሉ ማቆየት መቻልን፣ ማስቻልን በእንስራ የተቀበረ ማር፣ ቅቤ፣ የጽሑፍ ሀብት ወይም ሌላውም ተቀብሮ የተቀበረበት ቦታ እና ሁኔታ ብራና ላይ ተጽፎ በክታብ መልክ ተሰፍቶ ወራሽ አንገት ላይ ይንጠለጠላል። ወራሽ ሲፈልግ አውጥቶ ያየዋል፤ ወይም ክታቡን አድሶ ለትውልድ ያስተላልፋል። ይህ የደራሲው ፈጠራ አይመስለኝም ነባሩን ባህል ፈትሸው ያሳወቁበት ነው። አስረጅ እንዲሆነን በዐሥር ዓመቱ ምንልክ እጅ መስጠት ጊዜ አጼ ቴዎድሮስ አባትዎ ምን አወረሱህ? ቢሉዋቸው ክታባቸውን አሳዩ። ወታደሮቹም ክታቡን ከአንገታቸው ላይ በጥሰው ብራናው ቢነበብ ሀብቱ ልኩና ያለበት ቦታ ታወቀ። አሸናፊዎቹ ወታደሮችም ሀብቱን ተከፋፈሉት ይሉናል የታሪክ ጸሐፊው ተክለ ጻድቅ መኩሪያ።
እንደ ፍቅር እስከ መቃብሯ "ሰብለ ወንጌል" ሁሉ የእንስራው ዋና እንስት ገጸ ባህሪ "የኔዓለም" ስትሰኝ የኔዓለም እንደ ሰብለ ወንጌል የረጋውን ነባሩን ሥርዐት ክፉኛ ተፈታትናዋለች። በሕይወቷም ድል ቀንቷታል። የፍቅር እስከ መቃብሯ ሰብለ ወንጌል ለእምነቷና ለፍቅሯ ስትሰዋ የእንስራዋ የኔዓለም ለእምነቷ ለመርሆዎቿ ኖራ በድል አድራጊነት ተወጥታ እድሜ ጠገብ ሆና ስታልፍ ነው የምናየው። ይህ ባህልን ዘልማዳዊ እምነትን እና ሃይማኖታዊ ትውፊትን በአዎንታዊ መልኩ መለወጥና እድገትን ማሳየት እንደሚቻል የታየበት መጽሐፍ ነው።
ሌላው ትኩረቴን የሳበው ደራሲው በቴዎድሮስ ዘመን የነበረውን ባህላዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ንቅናቄና ቀውስን፣ ድቀትን፣ ድህነትን፣ የኑሮ መመሰቃቀልን ዘመናት አሻግረው በኢህአዴግ ዘመን ከተፈጠረ ባህላዊ ማኅበረሰባዊ ንቅናቄና ቀውስ ጋራ አመሳክረን፣ አንጥረን እንድናይ ዘመናትን ትውልዶችን አሻግረው ያዛነቁበት መንገድ ደግመን ደጋግመን አገራችን ላይ ማኅበረሰቡ ላይ የደረሰውን ቀውስ እንድናስታውስ እንድንቆዝም ጋባዥ ነው።

ከታሪክ አንጻር

ታሪክ ዝርዝር ውስጥ ከመግባታችን በፊት የአብዛኛው ገጸ ባህርያት ስም ታሪካዊ የሰው ስሞች ናቸው። ለምሳሌ የኔሰው ገብሬ፣ ገብርዬ (ገብረሕይወት ጎሹ) ወዘተ…
ሌላው እርግጠኛ ሆኜ ቅድመ ኢህአዴግ ትውልዶች የአፄ ቴዎድሮስን የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ተምረውት እንዳለፉ ሁሉ፣ በኢህአዴግ ዘመን የተወለዱም ቢሆኑ፣ የተማሩም አንባቢ ወገኖች የቴዎድሮስን የንግሥና ታሪክ ያውቁታል ብዬ እገምታለሁ።
አፄ ቴዎድሮስ እና ታሪካቸው ሲነሳ ሀቲቶቹ የሚያተኩሩት ሀገሪቷን ከዘመነ መሳፍንት ያላቀቁ መሆናቸው፤ ቴክኖሎጂ ሀገር በቀል እንዲሆን መጣራቸው፤ ጦረኝነታቸው፣ ጀግንነታቸው፣ ከካህናት ጋራ የነበራቸው ግብግብ፣ ከእንግሊዝ ጋራ ለመዋጋት መቅደላን የጦር ከተማቸው ማድረጋቸው ብዙ የመጻሕፍት እና ባህላዊ ቁሶች ማከማቻ ማድረጋቸው በመጨረሻም ሕይወታቸው በራሳቸው እጅ ማለፉን ነው።

የእንስራው የቴዎድሮስ ዘመን እይታ ዋነኛ ትኩረቱ እሳቸው ሕዝብን የሚያዳምጡበት የመገናኛ መንገድና፣ አሁን በሰለጠነው ዘመን ብሄራዊ መዛግብትና መጻሕፍት ቤት የምንለውን እሳቤ ለመፍጠር የሞከሩ፣ ብዙ መጻሕፍት ያሰባሰቡ መሪ ነበሩ። መጻሕፍቱ መቅደላ ላይ መዘረፋቸው የታወቀ የታሪክ ሀቲት ነው።
መጻሕፍት ስንል ህትመት/ ወረቀት ሊመስለን ይችላል። መጽሐፍ በዚያ ዘመን በእጅ የሚጻፍ፣ የሚገለበጥ፣ መጻፊያ ቀለሙም በእውቅ የሚበጠበጥ፤መጻፊያ ሰሌዳውም ከቤት እንስሳት ቆዳ ተፍቆ የሚዘጋጅ ብራና ሲሆን መደጎሻውም፣ መጽሐፉ ብልና አይጥ እንዳይበላውም በውርዘት እንዳይበላሽም የሚጠበቅበት የራሱ የሆነ ሥርዐት የነበረውና የመጻሕፍት ምርት ውስብስብ የእደ ጥበብ ውጤት ነው።

ቴዎድሮስ የብራና መጻሕፍቱን ራሳቸው ከማጻፋቸው፣ ከማስገልበጣቸውም በተጨማሪ በግዢ ያሰባሰቡባቸው ዘዴዎች፣ መንገዶች፣ ከባለንብረቶቹ በዋንኛነት ከየገዳማቱና አድባራቱ ጋራ ያካሄዱዋቸው አታካች ድርድሮች አስደናቂ በሆነ መልኩ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እናገኛቸዋለን። መጻሕፍት ከነዚህ ምንጮች መሰብሰብ መቻላቸውም እንኩዋን ያኔ አይደለም አሁንም ባለን ባህል የምናውቀው አድካሚ ተግባር ነው። ይህንን የመዛግብትና የመጻሕፍት ግምጃ ታሪክ ዝርዝር ባለና ማራኪ በሆነ መልኩ ደራሲው አንዱዓለም ጽፈውታል። መጽሐፉንም ታሪካዊ ልብወለድ ያሰኘው በዋነኛነት ይህ የመጽሐፉ ክፍል ነው።
መጽሐፉን ከማኅበራዊ እና ግለሰባዊ-ስነ-ልቡና ከስነ ቋንቋ፣ እንዲሁም ከስነ ጽሑፍ የእውቀት ዘርፎች አንፃር ማየት ቢቻልም ከስነ ቋንቋ አንጻር የእኔን ምልከታ በአጭሩ አጋራና ለመጽሐፉ ስነ ጽሑፋዊ እይታ የስነ ጽሑፍ መምህሩና ምሁሩ የዘሪሁን አስፋውን መጣጥፍ እናያለን።

ከስነ ቋንቋ አንጻር

የመጽሐፉ የጽሑፍ ጥራት እና ስህተት አልባነትአስደናቂ ነው። ታሪክ ነክ መጻሕፍት በቅርቡ አንብቤ ነበር። አንዱ መጽሐፉ ከመግቢያው ጀምሮ አስደንጋጭ የፊደል ግድፈቶችና ስህተቶች የታጨቁበት ሆነው ሌላው መጽሐፉ ደግሞ ዐማርኛው ጥሩ የሆነ ግን መጽሐፉ ውስጥ የተሰነቃቀሩት የእንግሊዝኛ ቃላት በሚያስገርም መልኩ ብዙ ግድፈቶች ያካተተ ነበር፤ የሁለተኛው መጽሐፍ ደራሲ አውቆ አድርጎት ይሆን እንዴ ብዬ ከራሴም ጋራ ሞግቻለሁ። ይህ ሁለተኛው መጽሐፍ ስለ ዐማርኛው ስለ ቋንቋው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲወራ ጥራቱ "ልክ ዳያስፖራ እንደሚታተሙ መጻሕፍት ልቅም ያለ ነው።" የሚል አገላለጽ አይቼ በአእምሮዬ ሽው ያለው ሀሳብ በሀገር ቤት የሚታተሙ መጻሕፍት ያ ሁሉ አርታኢ ባለበት ሀገር እንዴት የመጻሕፍት የቋንቋቸው ጥራት ሊወርድ ቻለ? ግድ የለሽነቱስ ከምን መጣ? ሲሆን የደራሲዎቹስ ችግሮች ምን ይሆኑ? የሚል ሀሳብም ማሰላሰል ጀምሬያለሁ።
እንስራው በዳያስፖራ ጸሐፊ ግን ሀገር ቤት የታተመ፤ ሀገር ቤት ባለ አርታኢ በጥራት የተዘጋጀ፤ በጽሑፋዊ ውበቱም ሆነ በመጽሐፋዊ ዝግጅቱ ግሩም ሲሆን ትውልድ ተሻጋሪነቱን የሚያሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ሌላው ስነ ቋንቋዊ እይታ

የእንስራው መቼት በዋነኛነት ጎንደር-አዘዞ ስለሆነ የአካባቢውን ቀበልኛ አገላለጽ ድንቅ በሚያሰኝ መልኩ ደራሲው ተገልግሎበታል። ይህ ማለት የጎንደርን ዘዬን፣ የጎንደርን ዐማርኛ ሊያጠና ሊያውቅ ለሚፈልግ ተመራማሪ እንስራው ጥሩ ግብአት ጥሩ ዋቢ መጽሐፍ ነው።
ብዙ ሀሳቦችና አገላለጾች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለተማረ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለሠራ፣ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለሚያስብ ሰው ለማንበብ ሊያስቸግር በሚችል ደረጃ የመጽሐፉ የዐማርኛ አጠቃቀም ቱባ -ኦሪጅናሌ ነው። ይህንን በአንድ ሁለት ምሳሌ ማሳየት ፋይዳውን ያሳንስብኝ ይሆን እያልኩ ከመስጋት ውጪ፣ እንስራው የእንስራው የቋንቋ አጠቃቀም በድህረ ምረቃ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች ጥልቅ ጥናቶች ሊሠሩበት እንደሚችል ሙሉ እምነት አለኝ።

ከስነ ጽሑፍ አንጻር

ቀደም ብዬ እንዳተትኩት ዘሪሁን አስፋው "እንስራውን ሳነብ" በሚል ርዕስ ለመጽሐፉ ዳሰሳዊ መግቢያ ጽፏል። አስተማሪ ነው ብዬ ስላመንኩ እሱን አብረን እንይ።
"እንስራው በስምንት ዐበይት ክፍሎች የተዋቀረ ታሪክ ቀመስ ረጅም ልብ ወለድ ነው። በልብ ወለዱ ውስጥ የአገር ታሪክ አለ፤ ጀግንነትና ቆራጥነት አለ፤ ኢትዮጵያነት አለ። ጣፋጭና መራራ ሕይወት ይታያል። ክፉ ጊዜና ደግ ጊዜም ይታያል። የመተሳሰብ፣ የአብሮነት፣ የአንድነት፣ ገጽታዎች በግለሰብም፣ በማሕበርም፣ በአገርም ተንጸባርቀዋል፡፡ የራስን ወግና ልማድ አጠቃላይ ባህልን ይዞ መጓዝ እናም ለተከታይ ትውልድ የማስተላለፍ ተግባር በልብ ወለዱ በተቀረጹ ገጸ ባህርያት የዕለት ተዕለት ሕይወት ወጥ አንድ ዐቢይ ጉዳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለአንድነት ታጥቆ የተነሳው መይሳው ካሳ፣ አፄ ቴዎድሮስ አገሬ በባዕድ እጅ አትወድቅም ብሎ ያደረገው መራራ ትግልና የከፈለው መስዋዕትነት በአገራችን የኪነ ጥበብ ጎራ በተለያዩ ከያንያን ሲሳል የኖረ አሁንም ያለ ወደፊትም የሚኖር ትልቅ ገጽ ነው፡፡ በስነ ግጥም፣ በተውኔት፣ በስነ ስዕል፣ በረጅም ልብ ወለድ ምስለ ቴዎድሮስ እንደከያኒያኑ ፈለገ ምናብ ተስሏል፡፡ በረጅም ልብ ወለድ ዘውግ የብርሃኑ ዘሪሁን እና የአቤ ጉበኛ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለዶች ይታወሱኛል።
እነሆ ዛሬ ደግሞ አንዱዓለም ተፈራ ለየት ባለ አተያይና ለየት ባለ የታሪክ ቅንብብ ቴዎድሮስንና የቴዎድሮስን ዘመን ኢትዮጵያ ገጸ ጥንት በእንስራው ሳለልን፡፡ በእንስራው ውስጥ አያሌ ኢትዮጵያዊ መልኮችና እኛነቶች ከእውኑ ታሪክ ጋር ተዛንቀው ነው የተቀረጹት፡፡ ድርሰቱ በበቀለበት መቼት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ሕይወቱን ለማቆየት፣ ኑሮውን ለመግፋት የሚያደርጋቸው ውጣ ውረዶች ርስበርስ መደጋገፍ፣ ከአገሩ መሬት ጋር ያለው ጠባቃ ቁርኝት ልፋቱና እንግልቱ በአንድ ጎን ይታያሉ። በወዲያኛው በኩል ደግሞ ከበላዮቹ፣ ጊዜ ኃይልና ስልጣን ከሰጣቸውና ዘመኑ የኛ ብቻ ነው ከሚሉ የሚወርድበትን አስመራሪ ድርጊት ለማምለጥ የሚያደርጋቸውን ትግሎች እናያለን፡፡ የወደፊቱ ብሩህ ይሆናል ተስፋም ይታይበታል።
ሀገረ ሰባዊ ልማዱ፣ ቁሳዊ ባህሉ፣ ስነ ቃሉና ሀገረ ሰባዊ ህክምናው ልብ ወለዱን ለማበልጸግ እና ሕይወትን ከነለዛው ለማሳየት ተመርጠው ገብተዋል። የገጸ ባህርያቱ ውሎ አምሽቶት በዝርዝር ቀርቧል። አገሬው ለቀየው፤ ለደብሩ፤ በትልቁ ደግሞ ለአገሩ ያለውን ውዴታ እናይበታለን፡፡ ብዙ የአኗኗር መልኮች ከእውኑ ታሪክ ጋር ተዛንቀው በመቅረባቸው ድርሰቱ የነበረውን እንድናውቅ፤ ያለውን እንድንመረምርና የወደፊቱን እንድናስብበት የማድረግ ባህሪ ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የገጸ ባህርያቱን የእለት ተእለት ኑሯዊ መልክ በማሳየት፣ ከታችኛውም ሆነ ከላይኛው ማሕበረሰባዊ እርከን ጋር በመመካከር፣ በመከባበርና በመደማመጥ በአገር መኖር ያለውን ከፍ ያለ ፋይዳ ያሳያል፡፡
በድርሰቱ የተገለጹት ማሕበረሰባዊ እሴቶች ለአብሮነትና ለአንድነት ያላቸውን አስተዋጽኦ እናያለን፡፡ እሴቶቹ በአንዳንድ ዘመናት ተሰብረው አገሬውን የጎዱ፣ ኑሮውን የበጠበጡ፣ የከፉ፣ ክስተቶች ተፈጥረው እንደነበር እና እነዚህን አስወግዶ በተሻለ ለመተካት የተደረጉ ትግሎችንም በራሱ ስልት ደራሲው አሳይቶናል፡፡ ለአንድነትና ለመልካም አገራዊ የጋራ ሕይወት የታገሉና የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ቁርጠኛ ገጸ ባህርያትንም ቀርጾልናል፡፡ ወዲህ ወደ ቅርቡ ዘመነ ኢትዮጵያ መጥቶ ደግሞ ባለፉት የቅርብ አሰርታት ኢትዮጵያውያን ያሳለፉትን ውጣውረድና እንግልት አሳይቶናል፡፡ በመረጠው ልቦለዳዊ መዋቅርና የትረካ ቅጥ የጥንቱንም የቅርቡንም ታሪከ አገር በየዘመኑ ከነበረው ማሕበረሰባዊ ሕይወት ጋር አዛንቆ ጽፎታል፡፡
በልብ ወለዱ ውስጥ የተሳሉት ገጸ ባህርያት የመቼታቸውን ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ የራሳቸውን ዘዬ በመናገራቸውም ድርሰቱ እውናዊነትን ለዛና መዓዛን አግኝቷል፡፡ የአረፍተ ነገሮቹ አጫጭርና ልከኛ መሆን ንባባችን እንዳይደነቃቀፍ አግዟል፡፡ እንስራው በአንደኛ መደብ እኔ ባይ የትረካ አንጻር የቀረበ ነው፡፡ ይህ አይነቱ አንጻር ለአያያዝ ከባድና ፈታኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አንዱዓለም የትረካ አንጻሩ ሊያስከትል እሚችለውን ሳንካ ተቋቁሞ ተነባቢ ድርሰት የጻፈ መሆኑን ተመልክቻለሁ፡፡ ለዚህም እሰይ እንኳን ቻልክበት እለዋለሁ! (ዘሪሁን አስፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ፣ ስነ ጽሁፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት)"]

ይህንን ዘመን ተሻጋሪ በእንግሊዝኛ classic book ደረጃ ያለው መጽሐፍ በቅርቡ ተገቢውን ቦታ ያገኛል ብዬ አስባለሁ። ደግሞም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ተገቢውን ስፍራውን ማግኘቱ አይቀርም። እድለኛ ኾኜ፣ እንስራውን፣ መጽሐፉን ለማንበብ ችያለሁ። በማንበቤም ደስተኛ ነኝ። ይህንን ድንቅ መጽሐፍ ለኢትዮጵያ ታሪክ ለዐማርኛ ቋንቋ እና ለዐማርኛ ስነ ጽሑፍ ማንጥሪያ መመዘኛ እንደነ ዳኛቸው ወርቁ፣ አዳም ረታና ሐዲስ ዓለማዬሁ መጻሕፍት ወደረኛ አግኝተናል። ደራሲውን አንዱዓለም ተፈራን እጅ እነሳለሁ።

Reviewer :- © Daniel Aberra (Independent Scholar
MA in Linguistics from Addis Ababa University, MSc in Linguistics from University of Alberta) is an associate editor at ©Think Ethiopia

የአዕምሮ ዕውቀት ብቻውን በጎ ሰው አያደርግም!
(እ.ብ.ይ.)

አላዋቂ መሆን ቀላል ነው፤ አለማሰብ አይከብድም፡፡ ደነዝ መሆን እውቀት አይሻም፡፡ ዓላማ ቢስ መሆን አያስቸግርም፡፡ ድንቁርና ወጪ የለውም፡፡ ጨካኝ ለመሆን የሮኬት ሳይንስ ማጥናት አይጠበቅብህም፡፡ ሰው ላይ ክፋት ለመፈፀም የተለየ ችሎታ አይፈልግም፡፡ አድፍጠህ፣ ተደብቀህ፣ ጨለማን ተገን አድርገህ ሰው ላይ ጉዳት ማድረስ ልዩ ክህሎት አይሻም፡፡ የውሸት ወሬ ፈጥረህ ሰውን ከሰው ማጋጨት፣ ትዳር መበተን፤ ወዳጅነትን ማበላሸት፤ ፍቅርን ማርከስ ስማርት መሆን አይጠይቅም፡፡ ክፉ ለመሆን ዋና መስፈርቱ አለማሰብ ነው፡፡ ጨካኝ ለመሆን የሚጠበቅብህም ህሊና ቢስ መሆን ነው፡፡ ለመሸምጠጥ፣ ቃልህን ለማጠፍ፣ አደራህን ለመብላት ምንም የምትወጣው ዳገት፤ የምትወርደው ቁልቁለት የለም፡፡ የሰውን ልብ ለመስበር፣ ተስፋውን ለመንጠቅ፤ ህልሙን ለመቀማት፤ ዓላማውን ለማደናቀፍ ዩንቨርስቲ መግባት አያስፈልግህም፡፡ የሚያስፈልግህ እፍረተ-ቢስ መሆን ብቻ ነው፡፡ ሕሊናህን ለመሸጥ፤ ሞራልህን ለማውደም፣ ሰውነትህን አሽቀንጥረህ ለመጣል፤ በሆድህ ለመውደቅ አለማሰብ በቂ ነው፡፡

ፕሌቶ ‹‹አብዛኛው ሰው ሌላ ሰውን በቀላሉ ሊጎዳ ይችላል፡፡ ነገር ግን ማንም ሰው በቀላሉ በጎ ስራ መስራት አይችልም፡፡ (Any man may easily harm, but not every man can do good to another)›› የሚለው ለዚህ ነው፡፡ አንዳንዶች መልካምነት ቀላል ነው ይላሉ፡፡ እኔ ግን አልስማማም፡፡ መልካምነት ከባድ ነው ባይ ነኝ፡፡ በዚህ ‹‹እኔ ብቻ›› በሚቀነቀንባት ዓለምና ዘመን ውስጥ መልካም ሰው ሆኖ መገኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ መልካምነት የሃሳብ ውጣ-ውረድ አለው፤ ማንም ዘው ብሎ የሚገባበት አይደለም፡፡ መልካምነት ዕውቀት ይፈልጋል፡፡ መልካምነት ከሌለህ ላይ መስጠትን ግድ ይላል፡፡ መልካምነት ከራስ ማለፍን ይሻል፡፡ መልካምነት ከእውነት ጋር ያጣብቃል፡፡ መልካምነት ያለአጃቢ፣ ያለአጭብጫቢ፣ ያለደጋፊ “ብቻን-መቆም” ይጠይቃል፡፡ መልካምነት ላለውም ለሌውም፤ ለተራውም ለባለስልጣኑም፤ ለሐብታም ልጁም፤ ለድሀአደጉም እኩል ማሰብን ይፈልጋል፡፡ መልካምነት ያለፍትሐዊነት ዋጋ የለውም፡፡ መልካምነት ከሆድ ይልቅ ህሊናን ያስቀድማል፡፡ ቅን አሳቢ መሆን የቤት-ስራው ብዙ ነው፡፡ አዋቂ ለመሆን ከራስ ሃሳብ ጋር ውጊያ መግጠም ያስገድዳል፡፡ ከአጉል ባህሉ፣ ከዘልማድ አስተሳሰቡ፣ ከአሉታዊ አመለካከቱ፤ ከዓለሙ ጋር የፊትለፊት ጦርነት መክፈት ይሻል፡፡ መልካምነት ራስንም ሌላውንም ከመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡ ሰው ሺ ዩንቨርስቲ ገብቶ ቢወጣ ከራሱ ጋር መነጋገር ካልጀመረ ውጫዊ እንጂ ውስጣዊ ዕውቀት አይኖረውም፤ ሌላውን ያውቃል እንጂ ራሱን አያውቅም፡፡ ስለቁሱ ይመራመራል እንጂ ስለመንፈሱ አይራቀቅም፡፡ በእንጀራ እውቀት ብቻ ሰው አዋቂ አይሆንም፡፡ የአዕምሮ ዕውቀት ብቻውን በጎ ሰው አያደርግም፡፡ በአዕምሮም፣ በስሜትም፣ በመንፈስም አዋቂ ለመሆን ራስንም፣ ሌላውንም የሚገነዘብ ደግ ልቦና ግድ ይላል፡፡ ለዚህ ነው አሜሪካዊዋ ፈላስፋ ማርታ ኑሳቡም (Martha Nussbaum) ‹‹ዕውቀት ለመልካም ባህሪ ዋስትና አይሆንም፤ አላዋቂነት ግን ለመጥፎ ባህሪ ምናባዊ ማረጋገጫ ነው (Knowledge is no guarantee of good behavior, but ignorance is a virtual guarantee of bad behavior.)›› የምትለን፡፡

ፕሌቶ ‹‹“ሁለት ዓይነት የነፍስ በሽታዎች አሉ፡፡ እነሱም የሞራል ውድቀትና ድንቁርና ናቸው፡፡ “There are two kinds of disease of the soul, vice and ignorance.”›› ይላል፡፡ እውነት ነው ብልህ ሰው ሞራሉ እንዳይወድቅ ዘወትር ሰውነቱን ያጎለብታል፤ አዕምሮውም እንዳይደነቁር መልካም ሃሳቦችን ለልቡ ይመግበዋል፡፡ በራሱ አሉታዊ ሃሳብ በሚፈጥረው በሽታ ነፍሱን አያሰቃይም፡፡ አስተዋይ ሰው ሃሳብን ከሃሳብ እያፋጨ አዲስ ሃሳብ ይፈጥራል እንጂ ሰዎችን እያጋጨ ከፀቡ በሚገኘው ትርፍ ስራ አይፈጥርም፡፡ ወሬ በማቀበል፣ ነገር በመስራት፣ ሴራ በመጎንጎን፤ ተንኮል በመቀመር፣ ክፋትን በመለማመድ ያልታመመ ጤነኛ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ጤነኛ ሰው ቆሻሻ ሃሳቡን ወዲያው ወዲያው ያስወግዳል፤ ክፉ ሃሳቦች በአዕምሮው ሲመላለሱ ቶሎ ብሎ ያፀዳቸዋል፡፡ ቅናትና ምቀኝነትን የሚጠነስሱ ስሜታዊ ሃሳቦች የአዕምሮውን ግድግዳ ጥሰው ሲገቡ ቀና ሃሳቦችን በመፍጠር ይዋጋቸዋል፡፡ የዲያብሎስ ውጊያ ይሉሃል ይሄ ነው!! የሃሳብ ጦርነቱ የመጀመሪያው ግንባር ከራስህ ጋር የሚደረገው ነውና!!

ወዳጄ ሆይ… አሜሪካዊው ፀሐፊና ገጣሚ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን ‹‹እውነት ከፍቅር የበለጠ እጅግ ውብ ነው፡፡ መልካምነትህ የእውነት ጠርዝ ከሌለው ዋጋ የለውም (Truth is handsomer than the affectation of love. Your goodness must have some edge to it, — else it is none.)›› እንዲል ዕውቀትህ መልካምነት፤ መልካምነትህ እውነት ይኑረው፡፡ መፅሐፈ ሲራክም ‹‹ደስም ቢለው ቢያዝንም የሰው ልቡ ፊቱን ይለውጠዋል፡፡ ደስ ያለው ልቦና ምልክቱ ብሩህ ገፅ ነው፡፡›› እንዲል ደስታ ከመልካምነትህና ከእውነተኛነትህ የምትለቅመው ጣፋጭ ፍሬ ነው፡፡ ብዙዎች ያገጥጣሉ እንጂ አይስቁም፡፡ በጥርሳቸው ሊሸውዱህ የሚሞክሩ ውስጡን ለቄስ የሆኑ ሺ ናቸው፡፡ ሳቃቸው ከጥርሳቸው የማያልፍ የትየለሌ ናቸው፡፡ እውነተኛዋን ሳቅ የሚስቋት ግን መንፈሳቸውን ያነቁ፣ ስሜታቸውን የገሩ፤ አዕምሯውን ያበለፀጉና ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው መልካም የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡

ቸር ጊዜ!

ደግ ስራ! እውነተኛ ዕውቀት!

ኢትዮጰያና ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑሩ!

____
© እሸቱ ብሩ ይትባረክ (እ.ብ.ይ.)
ሠኞ ጥር ፲፪ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም.

የአንድ የመዝገብ ቤት ጸሐፊ አሟሟት

የዋሁ ጸሐፊ ኢባን ዲሚትሩች ቼርቭያኮቭ በትያትሩ አዳራሽ በሁለተኛ ማዕረግ ተቀምጦ በኦፔራ መመልከቻ መነጽር እየታገዘ ሌ ክሎብ ደ ኮርንቬል የተባለውን ቲያትር ይመለከትባት የነበረች ያች ምሽት ድንቅ ምሽት ነበረች ።ቲያትሩን እያደነቀ በዚች ምድር ከሱ የተሻለ ደስተኛ ሰው እንዴሌለ አድርጎ አሰበ ።ድንገት ፊቱ ተጨማዶ ወደ ሰማይ አንጋጠጠና ዓይኑ ተገረጠረጠ።ትንፋሹ ቁርጥ ቁርጥ አለ ።ፊቱ ከኦፔራው መመልከቻ መነጽር ዘወር አደረገና ከመቀመጫው ብድግ ብሎ "አጢሹ!!" አለ ።በአንድ ቃል አነጠሰ ።

ማንም ሰዉ በየትም ቦታ ማነጠስ ይችላል ።ገበሬዎች ፣ፖሊሲ መኮንኖች ፣የተከበሩ ሰዎች እንኳን ያነጥሳሉ ።ማንም ይሁን ማን ያነጥሳል ።ቼርቭያኮቭም በዚህ አልተደናገጠም ።መሐረቡን አውጥቶ አፋንጫውን ጠራረገና እንደ ማንኛውም በመልካም ሥነ ምግባር እንደታነጸፀ ሰው ማስነጠሱን ያስቀየመው ሰው እንዳለ ወዲያና ወዲህ ተመለከተ ። በዚህ ገዜ ክፉኛ ደነገጠ።

እፊት ለፊቱ በመጀመሪያ ረድፍ የተቀመጠ አንድ ትንሽ በራ ሰውዬ እያጉረመረመ በእጅ ጓንቲው በራ ራሱንና አንገቱን ሲጠራርግ አየ ።
ቼርቭያኮቭ ሰውዬው የመገናኛ ሚኒስትሩ ጄኔራል ብሪዛሎቭ መሆኑን አወቀ ።

"በሳቸው ላይ ነው ያነጠስኩት?በእርግጥ አለቃዬ አይደሉም ፣ይሁን እንጂ መጥፎ ድርጊት ነው ።

ይቅርታ መጠየቅ አለብኝ" አለ ቼርቭያኮብ ።

ትንሽ እንደ መሳል ብሎ ወደፊት ጎንበስ አለና "ክቡር ሆይ ይቅርታ አድርጉልኝ! አስነጠስኩብዎት ..አውቄ አይደለም ..." አለ በሽክሹክታ ።

"ምንም አይደል "

"ይቅርታ አድርጉልኝ!እኔ ...ሆን ብዬ አይደለም!"

" እንዴት ያለ ነገር ነው ፣እባክህ ዝምበል ላዳምጥበት !"ቼርቭያኮቭ እነደመረበሽ አለ፣በድንጋጤ መልክ ፊቱን ፈገግ አደረገና
ሐሳቡን ወደ መድረኩ ለመመለስ ሞከረ ።

ተዋንያኑን ተመለከተ ።

አሁን ግን በዚች ዓለም ተደሳች መሆኑን አልሰማው አለ ።
ሰውነቱን ጸጸት ወረረው በትይዕንቶች መኻል ወደ ብሪዛሎቭ ጠጋ ብሎ ትንሽ ቆየት አለና በመጨረሻ ፍርሃቱን ዋጥ በማድረግ
" አሰነጠስኩብዎት አይደል?ጌታዬ ...ይቅርታ ያድርጉልኝ ...ዐውቄ አይደለም ..እባክዎን..."አለና አገተመተመ ።

"እውነቴን ነው የምልህ ..እኔ ረስቼዋለሁ ዝም ብለህ ብትመለከት?" አሉ ጄኔራሉ ፣ታችኛው ከንፈራቸው በንዴት እየተንቀጠቀጠ ።

"ረስቼዋለሁ ይላሉ አስተያየታቸው ግን አላማረኝም " አለ ቼርቭያኮቭ በጥርጣሬ ወደ ጄኔራሉ እየተመለከተ ።

"እኔን ማነጋገር አልፈለጉም ማለት ነው ።ሆኖም ዐውቄ እንዳላደኩ ማስረዳት አለብኝ ..ይህ የተፈጥሮ ሕግ ነው ።

አለበሊዝያ ዐውቄ ምራቄን የረጨሁባቸው ሊመስላቸው ይችላል ።
አሁን እንደዚያ ባያስቡም ቆይቶ ቂም መያዛቸው አይቀርም ?"
ቼርቭያኮቭ ወደ ቤቱ ከሄደ በኋላ የተፈፀመውን አስነዋሪ ድርጊት ለባቤቱ ነገራት ።

ባለቤቱ ገን ነገሩን በቀላሉ የወሰደችው መሰለው ። በርግጥ ለጊዜው ደነገጠች፣ብሪዛሎብ አለቃው አለመሆናቸውን ስላወቀች ወዲያው ተረጋጋች ።

"ቢሆንም ሔደህ ይቅርታ መጠየቅ ያለብህ ይመስለኛል ።አለበለዚያ በሕዝብ ዘንድ ሥነ ምግባር የጎደለህ ሊመስላቸው ይችላል" አለችው ።

ልክነሽ!ይቅርታ መጠየቅ ሞክሬ ነበር ፣ግን ልዩ አይነት ሰው ሆኑብኝ ። የኔ ይቅርታ መጠየቅ ስሜትም አልሰጣቸውም ።በዚያ ላይ ለማነጋገር ጊዚ አልበራቸውም "በሚቀጥለው ቀን ቼርቭያኮቭ አዲስ የደንብ ልብሱን ለብሶ ጸጉሩን ተስተከካለና ጥፋቱን ለመግለጽ ወደ ብሪዛሎቭ ሔደ። የጄኔራሉ የእንግዳ መቀበያ ቢሮ በአቤቱታ አቅራቢዎች ጢም ብሏል ። ጄኔራሉም የሰዎቹን አቤቱታዎች እየተቀበሉ እዚያው ክፍል ውሰጥ ነበሩ ። ጥቂት ሰዎች ካነጋገሩ በኋላ አይናቸውን ወደ ቼርቭያኮቭ ቀና አደረጉ ።

"ትላንት ማታ ክቡር ሆይ ያስታወሱት ይሆናል ።
በስሕተት አነጠስኩ ..ሳላውቅ ነው ያደረኩት ...ይቅርታ ..."እያለ ንግግሩ ጀመረ ።

"ውጣ ከዚህ ምን ጅሉ ነው !" አሉና ጀኔራሉ "ያንተስ ጉዳይ ምንድነው ?"አሉ የሚቀጥለው ሰውዬ ።

"እኔን አያዳምጡኝም ?"አለ ቼርቭያኮቭ ፊቱ ሳንባ እየመሰለ ።"ተቆጥተዋል ማለት ነው ...ችላ ብዬ የምተወው ጉዳይ አይደለም ...ማስረዳት አለብኝ .."
ጄኔራሉ ባለጉዳዮች አነጋግረው ከጨረሱ በኋላ ወደ ቤታቸው ጉዞ ሲጀምሩ ቼርቭያኮቭ እየገተመተመ ተከተላቸው ።
ክቡር ሆይ ! ይቅርታ ይደረግልኝ ።እንዲህ የማስቸግሮት ከልብ ስለ ተጸጸትኩ ነው እንጂ ሌላ አይደለም ..." ጄኔራሉ ሊሳደቡ ያሰቡ መስለው ተመለከቱትና ገፍትረውት ሔዱ ።

"ጌታው !ታሾፍብኛለህ?"አሉና በሩን እላዩ ላይ ዘጉ።

"ማሾፍ ? "አለ ቼርቭያኮቭ በሐሳቡ ።

ምንም የሚያስቅ ነገር አይታየኝም ።

አልገባቸውም እሳቸው አንድ ጄኔራል?ጥሩ ፣ከዚህ በኋላ እሳቸው የመሰለ ትልቅ ሰው ይቅርታ በመጠየቅ አልታክትም ።ገደል ይግቡ!! ደብዳቤ እጽፍላችኋለሁ እንጂ ከዚህ1በኋላ ዝርም አልላት !

ጨርሶ !አልመጣም ፣አበቃሁ !"

ቼርቭያኮቭ ወደ ቤቱ ሲጓዝ በአእምሮው የሚመላለስበት ይህ ነበር።

ደብዳቤውን ግን አልጻፈም ።

ደጋግሞ አሰበ ፣እንዴት መጻፍ እንዳለበት ሐሳብ ሊመጣለት አልቻለም ። ስለዚህ ሁኔታውን ለማቃናት በማግስቱ ወደ ጄኔራሉ መሄድ ነበረበት።

"ክቡር ሆይ!ትናንትና በድፍረት ያስቸገርኩዎት እርስዎ እንዳሉት ላሾፍብዎት አልነበረም "እያለ መናገር ጀመረ ፣ጀኔራሉ በመጠረጠር ትኩር ብለው ሲመለከቱት ፣"በማንጠሴ ላደረኩቦት በደል ይቅርታ ልጠይቅዎት ነው ...

በርስዎ ማሾፍ ግን ጨርሶ አላደርገውም ።

እንዴትስ ብዬ እደፍሮታለሁ?

በሰዎች ላይ ካሾፍንማ መከባበር ይጠፋል ....

የበላይ ማክበር አይኖርም "

"ወጊድ ከዚህ " አሉ ጄኔራል ፣በቁጣ እየተንቀጠቀጡ ።

ቼርቭያኮቭ በፍርሃት እየራደ

"ይቅርታ ያድርጉልኝ " በማለት የማንሾካሸክ ድምፅ አሰማ ።

"ውጣልኝ እኮ ነው የምልህ ?" አሉ ጄኔራሉ በእጝራቸው መሬት እየመቱ ።

ቼርቭያኮቭ ወሽመጡ ብጥስ አለ ።

ወደ ውጭ ሲወጣ መስማትም ማየትም ተሳነው ።
ወደ ጎዳናው ወጥቶ ጉዞ ጀመረ ።

በድኑን ወደ ቤቱ ተጉዞ እንዳለ ከነልብሱ ሶፋው ላይ ተዘረረ ፣ከዚያም ዐረፈ።

የአንቷን ቼኾብ ምርጥ አጫጭር ልብወለድ ታሪኮች

ትርጉም

በላይነህ አሠጉ
ጌታቸው በላቸው

ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት

1974

Dawit Bezabih

እድለኛ ሆኜ “When I am gone” የተሰኝው የመጀመሪያ መጽሐፌ ውስጥ የተካተተው ግጥሜ በደራሲ እና ተርጓሚ ቤተማርያም ተሾመ ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ ተተርጉሟል። እናንተም ግጥሙን ሰምታችሁ እንደምትደሰቱ አምናለሁ። መልካም እሁድ ❤️ በጣም አመሰግናለሁ Betemariam Teshome

WHEN I AM GONE
Tigest Samuel
ስሰናበት
ትርጉም ቤ.ማ.ተ
--------
ሞታለች ብለው ሲያውጁ -
አልቆ ሲያከትም እድሜዬ፣
ሁሉ በነበር ሲዘጋ -
ሲጠናቀቅ እሩጫዬ...
ተለይታ ስትሄድ ከ'ኔ -
ነፍሴ ለፍርድ ስትጠራ፣
አካሌ ከምድር ትቢያ -
ሲቀላቀል ከአቧራ...
ቀድመህ ትገኝ ይሆን ያኔ? -
እኔን ከፍ አ'ርጎ ለማንሳት?፣
በውብ ቋንቋ ውዳሴ -
'ባንደበትህ የቃል ትባት?
የማልሰማ፣የማልለማ -
ስሜት አልባ ሳለሁኝ ሙት፣
ደማቋ ፀሀይ ስትጨፈግግ -
እኔን ማስገረም ሲሳናት፣
ውቧ ጨረቃ ደብዝዛ -
አማላይ መልኳ ሲከዳት...
ስሜቱን ሲያጣ ስሜቴ -
ለክዋክብት ግድ ሳጣ፣
ሀሳቦችህ ቁብ ሳይሰጡኝ -
አፈንግጬ ዳር ስወጣ...
እነዚያ ውዳሴዎችህ -
መቼም ያልተዘመሩ፣
የፍቅር ቃል ሹክሹክታዎችህ -
ተደብቀው ያልተወሩ...
ይዘንቡ ይሆን እንደ ካፊያ -
እረጥብ ይሆን እርሼ?
ልቤ መምታትቱን ሲያቆም -
ዛሬ ሲቋረጥ ትንፋሼ?

ሕያው መሆኔ ሲያበቃ -
ከምድር በታች ስቀበር፣
ስጋዬን ምስጥ ሲበላው -
አጥንቴ ፈርሶ ሲፈረፈር...
ትሆን ይሆን ቀዳሚ -
ያለህን ሁሉ ለመስጠት?
በበጎነት የተሞላህ -
የተረፈልህ ቸርነት?
ከመቃብር ድንጋዬ ላይ -
ይዘህ 'ያአበባ ጉንጉን፣
ከሞትኩ፣ከሄድኩኝ በሗላ -
አርፍደህ ቸር የምትሆን?

የቀብሬ አስፈፃሚ -
ሆነህ ድንገት ከተመረጥክ፣
እንዲህ እና እንዲያ ነበረች -
ብለህ ስለ'ኔ ከተናገርክ...
በተባ ቃል አንደበትህ -
መወድሴን ስትናገር፣
አደራህን ንገርልኝ -
እንደዚህ ብዬ እንደነበር።
"አሁን፣ ዛሬ ደግ ሁኑ - ቀን እያለ ተረዳዱ፣"
"ሕያዋንን አፍቅሩ እንጂ - ሙታኖችን አትውደዱ።"

WHEN I AM GONE

When they say I am deceased...
When my expiry date is stamped...
When my spirit is called for judgment..
When I am blended with earthly dust...
Will you be the first one to exalt me?
With your eloquent eulogy?
When I no longer hear or sense...
How is that for kindness?

When the sun ceases to amaze me...
When the moon is no longer euphoric...
When I stop caring for the stars...
When I am indifferent to your thoughts...
All your unsung songs of praise...
All your unsaid endearments...
Will they shower me after death?
When I no longer feel nor breathe?

When I stop being conscious...
Buried underneath the earth...
When worms eat my flesh and bones...
Will you be the first one to give?
Immerse in deeds of goodness?
Flowers on my grave?
Kindness after my death?

If you are the elected soul...
Handling my funeral...
And if you must talk about me...
With your eloquent eulogy...
Tell your audience that I said..
“Be kind now, in the moment...
Love all the living not the dead”

© Tigest Samuel

የ ጉ ለ ሌ ው ሰ ካ ራ ም
_ ♧ __

"A drunk mind speaks a sober heart."
— Jean-Jacques Rousseau

“የጉለሌው ሰካራም” የደራሲ ተመስገን ገብሬ አጭር ልብወለድ ሲሆን፣ ታትሞ የወጣው በህዳር 22 ቀን 1941 ዓ.ም.፣ (በነፃነት ማተሚያ ቤት)፣ አዲስ አበባ ነው፡፡

በእርግጥ ከዚያ በፊት በሀገራችን ሰዎች የተጻፉ ሌሎች ሥራዎች ቢኖሩም ብዙ የስነ ጽሑፍ ሐያሲያን ይህ የተመስገን ገብሬ “የጉለሌው ሰካራም” በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ አጭር ልብ ወለድ ድርሰት እንደሆነ ይናገሩለታል፡፡

መቼቱ አዲስ አበባ ከተማ፣ ጉለሌ ነው፡፡ መጠጥ ቤቷ ደሞ በሰባራ ባቡር፣ ከዮሐንስ ቤተክርስትያን አጠገብ የምትገኝ የበቀለች አምባዬ ግሮሰሪ ናት፡፡ ባለታሪኩ የጉለሌው ዝነኛ ሰካር ተበጀ ነው፡፡

ተበጀ - ከገፈርሳ እስከ ደጃዝማች ይገዙ ሰፈር ባለው ሰፊ ግዛቱ - በዶሮ ንግድ እጅጉን የታወቀ የዶሮ ነጋዴ ነው፡፡ እጅጉን የታወቀው በዶሮ ነጋዴነቱ ብቻ አይደለም፡፡ በስካር ዝናው ጭምር ነው፡፡

የተበጀ ስካር የየሰፈሩ የቡና ማጣጫ ሆኗል፡፡ እያንዳንዷ የማታውቀውም የምታውቀውም ሴት ቡና ሲኒ ይዛ ስትቀመጥ - ተበጀ ያደረገውንም ሌላ ሰው ያደረገውንም እየጨማመረች ተበጀ አደረገ ብላ አዳዲስ ግብር ትሰጠዋለች፡፡

እና ዝናው ጉለሌን አልፎ አዲስ አበባን አካሏል፡፡ እና ተበጀ ይሄን ሲያስብ በንዴት እንዲህ ይላል፡- "ጉለሌ ሥራው ወሬ ማቡካት ነው፣ የፈለገውን ያቡካ!"

በአጠቃላይ ግን - ሰካራም እየተባለ የሚያደርገው መልካም ተግባር ሁሉ ሳያውቀው እንዳደረገው እየተቆጠረ አመድ አፋሽ ሆኖ ቀረ እንጂ - ተበጀ መልካም ሰው ነው፡፡

አንዴ ወንዝ የገባችን ገረድ አድናለሁ ብሎ ራሱን ለጎርፍ አሳልፎ የሰጠ፣ ግን አሳማ ይዞ የወጣ - ለመልካም ግብ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ መልካም ሰው ነው፡፡

ራሱን ይጠይቃል፦ "የሰው ታላቅነቱ ምኑ ላይ ነው? መጠጥ ስላልጠጣ፣ ሚስት ስላገባ፣ ልጅ ስለወለደ፣ ሀብታም ወይም ደሃ ስለሆነ ነው? እኔ ከሙሉ ሰውነት ምን አጉድዬ፣ ምን አጥፍቼ ነው ይሄን ያህል ሁሉም ሰው እየተነሳ ‹‹ሰው ሁን!›› እያለ ሊመክረኝ የሚነሳው?" - እያለ ለራሱ፡፡

"እስቲ ሰው ልሁን" እያለ ለጋብቻ የጠየቃት ሴት ሁሉ ዝናውን ሰምታ በቁሙ ታሰናብተዋለች፡፡ የነፍስ አባቱ ሳይቀር - "ስካርህን ካላቆምክ አልባርክህም" ብለው - "ጉለሌ ያውጣህ!" ብለው ለቁም ገሃነም ጥለውት ሄደዋል!

ሁለተኛውን የነፍስ አባቱን ሁሌ እሁድ በመጣ ቁጥር አገኛቸዋለሁ ይላል - እርሱ ግን እሁድ ዕለት መገኛው - በከባድ ሀንጎቨር እየተጠቀጠቀ ከአልጋው ላይ!!

የተበጀ ህልምና የተበጀ እውን አልገናኝ ብለውት የተቸገረ - እና ብስጭቱን ለመርሳት፣ ወይ ለመስከር፣ ወይ ለመደሰት የሚጠጣ - እና የሚስቅ፣ የሚጮኽ - እና ደግሞ ተመልሶ የሚፀፀት - ባህርየ-ሰብዕ ነው - የጉለሌው ሰካራም!

ተበጀ መጠጥን ብዙ ጊዜ ለማቆም ከራሱ ጋር መሐላ ፈጽሟል፣ በበነጋው ግን ያው ነው፡፡ ውስኪ! ውስኪ ከነጠርሙሱ ነው የተበጀ ምሱ! በሰካርነቱ ያልደረሰበት ውርደት የለም! ሰክሮ ያልወደቀበት መንገድ የለም! በሰከረበት ዝናብ ወስዶት እሳት አደጋ ተጠርቶ አንስቶት ያውቃል፡፡

የጉለሌ ህዝብ ከወደቀበት ቦይ ተረባርቦ ያነሳዋል፡፡ እርሱ በማግስቱ ወደ ሥራው ይገባል፡፡ ለውለታው ተበጀ "የጉለሌ ልጅ ነኝ!" ይላል፡፡ "ደሃም ሆንን ሃብታም፣ ሰካራምም ሆንን ህርመኛ - ሁላችንም አባታችን ጉለሌ ነው!" እያለ ይፎክራል፡፡

ፀጉሩን መቀስ አስነክቶት አያውቅም፡፡ መጠጥና ትምባሆ፣ እና ሳቅና ጩኸት - አይለዩትም፡፡

"ደብረሊባኖስ ገዳም ብትገባ የሚጠብቅህ
ዝምታ ነው፣ ወፍ እንኳን ጩኸት የላትም፣
ባህታውያኑ ውሃ ይጣፍጣቸዋል - ሰካራም
ምን ልክፍት አምጥቶበት ነው የመረረ ጌሾና
ብቅል የሚጋተው እና የሚጮኸው?"

እያለ ያውጃል የጉለሌው ሰካራም - ተበጀ፡፡ ራሱን ይኮንናል፣ በራሱ ይሳለቃል፡፡ ውሃ እንዲጣፍጠውም ይመኛል፡፡ ግን ከአልኮል መጠጥ መላቀቅ አልሆንለት አለ፡፡

በመጨረሻ አንድ ባለ ዳስ ጎጆ ይሰራና - በቤቱ ኩራዝና ክብሪት ከአልኮል መጠጥ ጋር ይዞ ይገባል፡፡ ሲያስበው "መጠጥና እሳት ባንድ ቤት መግባት የለበትም" ይላል ለራሱ፡፡

ሰክሮ ቤቱን ቢያቃጥለውና አመዱ ቢወጣ - "እዚህ ጋር አንድ ጎጆ የነበረው ሰካራም ነበረ…" እያለ የጉለሌ ሰው እየተጠቋቆመ እስከ ዘለዓለሙ ሲስቅበት ሊኖር ነው፡፡ የጉለሌው ሰካራም - ለቤቱ ክብር ሲል - መጠጥ ለማቆም ወስኖ - ለአንድ ዓመት፣ ከ9 ወር፣ ከ9 ቀን፣ አቆመ፡፡

እና በዓመት ከ9 ወር፣ በ9ኛ ቀኑ ግን - ወደ መጠጥ ቤት ሲሄድ - የናፈቁት ወገኖቹ እንደ ሀገር መሪ ባለ እልልታና ሆታ ሲቀበሉት - መልሶ ሰክሮ ባቡር ሃዲድ ላይ ወደቀ። ባቡር እግሮቹን ደፈጠጣቸው።

ከእርሱ ጎን የተደፈጠጠ አህያንም አሞሮች ሲቀራመቱት - ሃኪም ጋር ሄዶ "እግሩ ይቆረጥ" ሲባል - ሃኪሞቹ "እስከ ጉልበቱ ከቆረጥነው የእንጨት እግር አስገብቶ ለመጠጣት ስለሚወጣ - እስከ ቂጡ አስጠግተን እንቁረጠው" ተባብለው ሲቆርጡት - እንደ ሰመመን ሆኖ ይሰማዋል።

እግሮቹን መዝኑና አስታቅፉት ተብሎ - 10 ኪሎ እግር ሲያስታቅፉት - ወዘተ - እነዚህ ሁሉ አስፈሪ ትዕይንቶች ይቀያየራሉ። እና በመጨረሻ - ህልም ይሁን እውን ተቸግሮ ይጠይቃል። የጉለሌው ሰካራም፦

“ስንት እግር ነው ያለኝ?”

“ስንት እግር ነው ያለኝ?”

የቤቱ ገረድ ይመልሱለታል፡-

“ልጆቼን ያሳደገችው ላም አራት እግር ነው ያላት…!”፡፡

ይሄ የደራሲ ተመስገን ገብሬ ኢትዮጵያዊ ቀደምት አጭር ልብወለድ በጨዋታ የተዋዛ አቀራረብ ያለው፣ የማይሰለች፣ የሰውን ውስጣዊ ስነልቦናና ማንነት ዘልቆ የሚያይ፣ ማኅበረሰባችንን ጠንቅቆ የተረዳ፣ እና በድንቅ ሚዛናዊ ሥፍራ ላይ ሆኖ የገጸባኅርያቱን እሳቤና ድርጊት የሚተርክ - እጅግ ሸግዬ ዘመናዊ የፈጠራ ጥበብ ውጤት ነው፡፡

እና ደግሞ እንደ አንድ ድንቅ የጥበብ ሥራ አዲስ ግዙፍ ነፍስን ከመንገድ ዳር መዝዞ፣ ሥጋ አላብሶ፣ ነፍስ ዘርቶ፣ እያጠጣና እያናገረ በህሊናችን አይረሴ የሆነ በቅርብ የምናውቀውን ሰው ይከስትልናል።

እንደ ሞናሊዛ፣ እንደ ዶን ኪኾቴ፣ እንደ ጉዱ ካሣ፣ እንደ አባ ዓለም-ለምኔ፣ እንደ ባለካፖርቱ አካኪ አካኪቪች። እንደ ታራስ ቡልባ። እንደ አደፍርስ። እንደ ሌሎችም ኃያል የብዕርና የቀለም ጋብቻ የወለዳቸው አይረሴ ፍጡራን። አንዴ "የጉለሌው ሰካራም"ን ያነበበም - ፈጽሞ አይረሳውም!

ምናልባትም - እንዲህ እንደ ተበጀ በግላጭ ዝነኛ አንሁንበት እንጂ - አሊያም እንዲህ ጨርሶ አይለይልን እንጂ - ሁላችንም ብንሆን - ሰው ነንና ጥቂት ጥቂት ተበጀነት አያጣንም። የጉለሌው ሠካራም በሁላችንም ውስጥ አለ።

በተለያዩ የሕይወት መስኮች ስንንከላወስ - ከምንሸሸው ነገር መውጣት አቅቶን - እየተፀፀትን ወደዚያው ወደምንኮንነው ነገር ደግመን ደጋግመን ለምንመላለስ ብዙ ሰዎች - ይሄ የጉለሌው ሰካራም ድርሰት በዘዋራ ሁነኛ መልዕክት የሚነግረን - እውነተኛ የውስጥ ደወል ነው!

በበኩሌ ተበጀ ውስጤ ነው! ይታየኛል በጉለሌ! በሰባራ ባቡር! በዮሐንስ! ባዲሳባ! በደጃች ይገዙ ሰፈር! በበቀለች አምባዬ ግሮሰሪ! ያውና እዚያ ማዶ - የጉለሌው ሰካራም! የሲሲፈሷ ህይወታችን መስታወት!

“የጉለሌው ሰካራም”። በደራሲ ተመስገን ገብሬ ከ67 ዓመታት በፊት (በኅዳር 1940 ዓ.ም.) የተፃፈ አጭር ልብወለድ።