ጄይሉ ቲቪበመርካቶ ሸማ ተራ የደረሰውን የእሳት አደጋ መንስኤ እየመረመረ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ
ጄይሉ ቲቪ ፣ ጥቅምት 12፣ 2017 ትናንትና ምሽት በአዲስ አበባ አዲስ ክፍለ ከተማ መርካቶ ሸማ ተራ አካባቢ ባጋጠመ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።
የአደጋውን መንስኤ ለማጣራት የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌዴራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ቡድን ጋር በመቀናጀት ምርመራ መጀመሩ ተጠቁሟል፡፡
አደጋውን ለመከላከልና በአደጋው ምክንያት ሌላ ወንጀል እንዳይፈፀም እንዲሁም የአደጋ ተከላከይ ሠራተኞች ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያጋጥም አስፈላጊው ርብርብ መደረጉ ተጠቁሟል፡፡
በዚህም የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የመከላከያ ሠራዊት፣ ሪፐብሊካን ጋርድ፣ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የሠላምና ፀጥታ መዋቅር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ሌሎች ተቋማት አደጋው እንዳይባባስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ነው የተገለጸው፡፡
አደጋውን እንደ ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የስርቆት ወንጀል የፈፀሙ 33 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የገለጸው ፖሊስ÷ ከአደጋው ጋር በተያያዘ በ7 ሰዎች ላይ ቀላል በ2 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱንም አመልክቷል፡፡
አደጋውን ለመከለከል የፀጥታና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም የአካባቢው ሕብረተሰብ ላደረገው ድጋፍና ተባባሪነት ፖሊስ ምስጋና አቅርቧል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ በደረሰው የእሳት አደጋ የተሰማውን ሃዘን ገልፆ፥ ወደፊት በምርመራ የደረሰበትን ውጤት ለህዝብ እንሚያሳውቅም በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡
ኤፍ ቢ ሲ