ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም (አቃቂ ቃሊቲ )
በ2ኛ ዙር የኮሪደር ልማት ምክንያት ከካሳንቺስ ተነስተው ወደ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 10 አሰተዳደር የመጡና ስራ የሌላቸው ነዋሪዎች በመረጡት የስራ ዘርፍ ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እንዲሰማሩ ለማስቻል ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ፣ ውብና ተመራጭ ለማድረግ በ2ኛ ዙር በኮሪደር ልማት ከካሳንቺስ ተነስተው ልማቱን ደግፈው ወደ ክ/ከተማው ለመጡ የልማት ተነሺ ነዋሪዎች በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ደማቅ አቀባበል እየተደረገላቸው ይገኛል።
በዛሬው ዕለትም ከካሳንቺስ ተነስተው ወደ ክ/ከተማው የመጡና ስራ የሌላቸው ነዋሪዎች በመረጡት የስራ ዘርፍ ስልጠና ወስደው ወደ ስራ እንዲሰማሩ ለማስቻል ያለመ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መርሃግብር ተከናዉኗል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ አስተዳደር ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የሥራ ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ውቢት ዮሐንስ እንዲሁም የወረዳ 10 አስተዳደር ዋና ስራ አሰፈፃሚ በመድረኩ ተገኝተው ለነዋሪዎቹ የእንኳን በደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ አስተዳደሩ ወደ ክ/ከተማው ለመጡ የልማት ተነሺዎች አካባቢያቸውን ፅዱ፣ ውብና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ከሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ጎን ለጎን ስራ ለሌላቸው ነዋሪዎች በመረጡት የስራ ዘርፍ ስልጠና ሰጥቶ ወደ ስራ እንዲሰማሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
ወ/ሮ ዉቢት አያይዞም የልማት ተነሺዎቹ በአካባቢዉ ያለዉን ፀጋ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎችን ጨምሮ በርካታ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን አሟጦ በመጠቀም ለነዋሪዎቹ የስራ ዕድልና ለኑሮ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የምዝገባ መስፈርቶችን በማሟላት ስራ ፈላጊ ነዋሪዎች ከሚቀጥለው ሰኞ ጥቅምት 18/ 2017ዓ.ም ጀምሮ በአቃቂ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ስልጠና እንደሚጀምሩ ተገልፀዋል።
በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ በርካታ ስራ የሌላቸው የልማት ተነሺ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በአስተዳደሩ እየተደረገላቸው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።